ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ባዘጋጀው የሥልጠናና የምክክር መርሐ ግብር ላይ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፦
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱሶ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅትና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ፤
ክቡራን የጠቅላይ ቤተክሆነት ኃላፊዎች፤
የዚህ ታሪካዊ ሥልጠና ተሳታፊዎች፤
ክቡራንና ክቡራት፤
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴ 5:16
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት የዕውቀት ምንጭ፣ የፍቅር ማኅደር፣ የሰላም ማዕከልና የታሪክ መዛግብት ሆና ኖራለች። ይሁን እንጂ ይህንን ታላቅና መልካም ሥራዋን፣ እንዲሁም በጨለማው ዓለም ውስጥ የምታበራውን መለኮታዊ ብርሃን ለዓለም ተደራሽ በሆነ መንገድ ማሳወቅና ማስመስከር የአሁኑ ዘመን ትውልድና በተለይም የእናንተ የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች ዋነኛ የሐዋርያነት ኃላፊነት ነው።
የምንኖርበት ዘመን የመረጃ ፍሰቱ እጅግ የፈጠነ፣ ነገር ግን እውነትና ሐሰት ተደባልቀው የሚቀርቡበት ውስብስብ ዘመን ነው። ዛሬ ላይ መረጃ እንደ ዋነኛ መሣሪያ እየተቆጠረ ባለበት ሰዓት፣ ቤተ ክርስቲያናችንም ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩባትን የተዛቡ ትረካዎችና ስም ማጥፋቶች የምትጋፈጠው በዋናነት በዚህ በሕዝብ ግንኙነት መድረክ ላይ ነው። ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን የሠራችው ታላቅ የልማት፣ የዕርቅ፣ የጥበብና የሀገርን አንድነት የማጽናት ሥራ በሚገባ ባለመነገሩና ባለመሰነዱ ምክንያት፣ ዓለም የእርሷን ባለውለታነት ዘንግቶ ፈተና ሊያደርስባት ሲሞክር ይስተዋላል። ይህ ክፍተት የተፈጠረው እኛ ብርሃናችንን በሰው ፊት በሚገባና በሚመጥን ቋንቋ ማብራት ባለመቻላችን ነው።
እስካሁን የነበረን የሕዝብ ግንኙነት አካሄድ በአብዛኛው ጥቃት ሲሰነዘርብን ምላሽ የመስጠት ወይም የመከላከል ባሕርይ የነበረው ነው። አሁን ግን ይህ አሠራር ሊቀየር ይገባል። እኛ አስቀድመን የቤተ ክርስቲያናችንን እውነት፣ መልካም ሥራና ሰላማዊ ማንነት ለሕዝብ በግልጽና በቅድሚያ ማሳየት አለብን።
የእኛ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ዓለማውያን እንደሚያደርጉት ውሸትን እውነት የማስመስከር ጥበብ አይደለም። የእኛ መሠረት እውነት እራሱ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ እውነትን በሙያዊ ብቃት፣ በወቅታዊ ቴክኖሎጂና በሰከነ መንፈሳዊ ጥበብ ማቅረብ ይኖርብናል።
ከስልጠናው የሚጠበቁ አበይት አቅጣጫዎች
ይህ ከየአህጉረ ስብከቱ የተሰበሰባችሁበት ታላቅ መድረክ፣ ዕውቀትና ክህሎታችሁን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን በአንድነት ለመቆም የሚያስችል የአውታረ መረብ መሠረት ለመጣል የተዘጋጀ ነው። ከዚህ ስልጠና በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታችሁ ስትመለሱ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች በተግባር እንድትርጎሙ
ለማሳሰብ እንወዳለን።
፩. የቅንጅትና የአንድነት አሠራርን መዘርጋት
የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መዋቅርና የአህጉረ ስብከቱ መዋቅሮች ልክ እንደ አንድ አካል ተሳስረው መሥራት ይኖርባቸዋል። በአንድ አህጉረ ስብከት ላይ የሚፈጠር ፈተና ወይም የሚመዘገብ ስኬት የሁላችንም ነው። መረጃዎችን በፍጥነት በመለዋወጥና በአንድ ድምፅ በመናገር የቤተ ክርስቲያናችንን ጥንካሬና አንድነት ለዓለም ማሳየት ይኖርባችኋል።
፪. ዘመናዊ የዲጂታል ሚዲያዎችን በአግባቡ መጠቀም
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የትውልዱ መገናኛና የሐሳብ መገበያያ ሆነዋል። እነዚህን መድረኮች በመልካም ሥነ ምግባር፣ በሳልና በጎ በሆነ ቋንቋ፣ እንዲሁም ማራኪ በሆኑ ዝግጅቶች በመጠቀም የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮና መልካም ሥራ ለዓለም ማሳወቅ አለባችሁ። ብዕራችሁ የሚገነባ እንጂ የሚያፈርስ መሆን የለበትም።
፫. ለዕርቅና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት
የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ምንጊዜም የሰላምና የዕርቅ ድምፅ ነው። በማኅበረሰቡ ውስጥ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሲፈጠሩ የእናንተ መግለጫዎችና ዘገባዎች ቁስልን የሚፈውሱ፣ ወንድማማችነትን የሚያጸኑና ሰላምን የሚሰብኩ ሊሆኑ ይገባል።
በመጨረሻም ይህ ስልጠና በቤተ ክርስቲያናችን የሕዝብ ግንኙነት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት፣ ራሳችንን እንድንፈትሽና በአዲስ መንፈሳዊ ጉልበት እንድንነሳ የሚያደርግ እንደሚሆን ያለንን ሙሉ እምነት እየገለጽን በዚህ ስልጠና ወቅት የምታገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር ለመጠበቅና የወንጌልን ብርሃን ለማዳረስ በትጋት እንድትሠሩ አባታዊ አደራችንን እናስተላልፋለን። በየአህጉረ ስብከቱ የሚመሩ ብፁዓን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳትም ለዚህ ሥራችሁ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉላችሁ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ እኛም በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደማናቋርጥ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።ይህንን ስልጠና በከፍተኛ ትጋት ላዘጋጁት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም እውቀታቸውንና ተሞክሯቸውን ለማካፈል እዚህ ለተገኙት አሰልጣኞች በሙሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ላቅ ያለ ምስጋናችንን እናቀርብላችኋለን።
ሐምሌ፱ቀን፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
አባ ሳዊሮስ
የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ
ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ