የተቀጸል ጽጌ (ዓፄ መስቀል) በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በታላቅ መፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ተከበረ ።
መስከረም ፲ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት ታሪካዊና መንፈሳዊ በዓላት አንዱ የሆነው የተቀጸል ጽጌ (ዓፄ መስቀል) በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ተከብሯል።
በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ሌሎችም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተገኙ ሲሆን፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የመምሪያ እና የድርጅት ሓላፊዎች ሊቀ ሥልጣናት አባ ሢራክ አድማሱ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የሀገር ባለውለታ የሆኑ አባትና እናት አርበኞችም በበዓሉ ላይ ተሳትፈዋል።
በዕለቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት፣ ከየአድባራቱ የመጡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያሬዳዊ «አጫብር» ዜማ አቅርበዋል። በተጨማሪም የቅድስት ሥላሴ የቅኔ መምህር የሆኑት ርዕሰ መዕምራን ዮሐንስ እና የአየር ማረፊያ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቅኔና መጻሕፍት መምህር መጋቤ ሐዲስ ኢሳይያስ ዕለቱን አስመልክተው ቅኔ አበርክተዋል ።
በመጨረሻም ብፁዕ ዲዮስቆሮስ በዚህ አስደናቂ የተፈጥሮ ዑደት በሊቃውንቱ ከታወጀ በኋላ፣ ያለፈውን ዓመት አመስግነው ዕለቱ የተቀጸል ጽጌ በዓል ብቻ ሳይሆን ከእሴይ ሥር የተገኘው የሕይወት ፍሬ የጌታችን እና መዳኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ተስፋ የሆነው የመስቀል በዓል የሚታወስበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የክረምቱ ወራት አልፎ ዝናቡ ሲቆም፣ ከአበቦቹ ፍካትና ከንቦቹ ትጋት በመማር እኛም ለመንግሥተ ሰማያት መግቢያ የሚሆን እምነትና መልካም ተግባር ልንሠራ እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል። ለምስጋና የተፈጠረውን አንደበታችንን ይዘን፣ አምላካችን በሚደሰትበት መንገድ ለቀጣዩ ዓመት በጸሎትና በሃይማኖት የታደሰ ሕይወት ሊኖረን እንደሚገባም አሳስበዋል
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቤንች ማጅ እና ከፋ ሸካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳ በአባታዊ ቃለ ምዳን እና ቡራኬ ተጠናቋል ።
«ተቀጸል ጽጌ» ማለት «አበባን ተቀዳጅ» ወይም «በአበባ አጌጥ» ማለት ነው። በዓሉ «ዓፄ መስቀል» በመባልም የሚታወቅ ሲሆን፣ የክረምቱ ወቅት አልፎ ምድር በአበቦችና በለምለም ሣር የምታጌጥበትን ጊዜ የሚገልጽ ነው።
በዓሉ ከክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ዓፄ ዳዊት የግማደ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ካመጡ በኋላ መስቀሉ ያረፈበትን ታሪክ የሚያወሳ ፤ ንግሥት ዕሌኒ እውነተኛውን የጌታችን መስቀል ከተቀበረበት አስወጥታ ካገኘች በኋላ ከተደረገው ታላቅ ደስታ ጋር ይያያዛል።
ተጨማሪ ፎቶ የአ/አ ሀ/ስ ሚዲያ ©የኢኦተቤመገናኛብዙኀንአገልግሎትሥርጭትድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency