ዳሽን ባንክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ለሚያገለግሉ አንዳንድ ሠራተኞች ለአዲሱ ዓመት መዋያ የሚሆን ሥጦታ አበረከተ፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዳሽን ባንክ በአበረከተው ስጦታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ክቡር አቶ አየለ ተሾመ የዳሽን ባንክ የስትራቴጂ ምክትል ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት “ዳሽን ባንክን በመወከል እንኳን ለ፳፻፲፱ ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፤ ዳሽን ባንክ ከተቋቋመበት አንዱ ዕሴቱ መካከል ኅብረተሰቡን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማገዝ ነው” ብለዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለውም “ለአዲስ ዓመት በኑሮ አነስተኛ ደረጃ ላሉ የኅብረተሰብ ወገኖቻችን የተለያዩ ድጋፎችን ስናደርግ ቆይተናል፤ ዛሬም እዚህ የተገኘነው በመንበረ ፓትርያርክ ለሚገኙ ወገኖቻችን ለበዓል እንኳን አደረሳችሁ ለማለትና መጠነኛ ስጦታ ለማበርከት ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም ይኸው ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያኗ ጎን ሆነን በሚያስፈልገው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ ነን” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “እንኳን ለ፳፻፲፱ ዓ.ም አዲሱ ዘመን በሰላምና በጤና አደረሰን፣ አደረሳችሁ፤ ዳሽን ባንክ ለወገኖቻችን መደገፍ አለብን ብላችሁ ስለመጣችሁ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ብፁዕነታቸውም አያይዘውም “ለወገኖቻችን ያደረጋችሁት ድጋፍ ቤተክርስቲያን ታመሰግናችኋለች እግዚአብሔር አምላክ ሥራችሁን ያቃናላችሁ፤ ከዚህ በበለጠ እንድታገለግሉ ያድርግልን፤ ዘመኑንም የሰላም፣ የበረከት፣ የአንድነት ያድርግልን” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
“ዳሽን ባንክ በሁሉም ሥፍራዎች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፤ ዛሬ እዚህ ስንመጣ ደስ ብሎናል” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ክቡር አቶ አየለ ተሾመ “በግቢው ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን አይተናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊት ብቻ ሳትሆን በጣም ብዙ የልማት ሥራዎችንም እንደምትሠራ፣ ኅብረተሰቡንም በብዙ ነገሮች እያገለገለች እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ይህን የልማት ሥራ ደግሞ ከፍ አድርጎ ለመሥራት ድጋፍ ያስፈልጋል፤ ዳሽን ባንክ በማንኛውም የባንክ አገልግሎት ለማገዝ ዝግጁ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕነታቸውም “መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ራስ ዋናው መሥሪያ ቤት መቀመጫ ግቢውን እያስዋብን የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን፤ ይህን ስንሠራ እንደናንተ ያሉ ሌሎችም እየረዱን፣ እያገዙን ነው፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ገዳም ቤተክርስቲን አጥር ሠርተውልናል፣ በመንበረ ፓትርያርክ ቅጽር ግቢ ለ50 ዓመታት በሌሎች ተይዞ የነበረውን ቦታ አስመልሰውልናል፤ የኮሪደር ልማት በሚሠራባቸው አብያተ ክርስቲያናት አካባቢም ርዳታ እያደረጉልን በመሆኑ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡” ብለዋል፡፡
በቅርቡም አዲሱ አዳራሽ ይመረቃል፤ በቀጣይ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ከዚህ በበለጠ ስለምንሠራ እንድታግዙን፤ ዛሬ በዚህ ተገኝታችሁ ላደረጋችሁልን ድጋፍ እናመሰግናለን ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡