በአህጉረ ስብከትና በማዕከል መካከል የተናበበ የሕዝብ ግንኙነት መዋቅር ለመፍጠር የሚያስችል ስልጠና መሰጠት ጀመረ”
ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.| ሕዝብ ግንኙነት መምሪያየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመረጃ ፍሰትን ተቋማዊና ዘመናዊ ቅርጽ ለማስያዝ ያለመው ፫ኛው ዙር አገር አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የሥልጠናና የምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት በጁፒተር ሆቴል በይፋ ተጀምሯል።
ሥልጠናውን በይፋ የከፈቱት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ድምፅ ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ መምሪያው በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸውን ሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ የሥልጠና አቅጣጫዎች ይፋ አድርገዋል፦
፩ኛ. ፈጣን መረጃ ፍሰት መዘርጋት፦ ወቅታዊና ተዓማኒ መረጃዎች ሳይዘገዩ በሁሉም የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሮች አማካኝነት በአንድ ጊዜ ለምእመናንና ለሕዝብ የሚደርሱበትን አሠራር መፍጠር።
፪ኛ. ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ ማዋል፦ ዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ለቅዱስ ወንጌል አገልግሎትና ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ገጽታ ግንባታ በአግባቡ መጠቀም።
፫ኛ. ተናበበ መዋቅር መፍጠር፦ የቤተ ክርስቲያንን ክብር በጠበቀ መልኩ፣ ሙያዊ ብቃትን ከሥነ-ምግባር ጋር ያጣመረና ከማዕከል እስከ አህጉረ ስብከት የተዘረጋ ጠንካራ መዋቅር ማደራጀት።
“የስልጠናው ዋና ዓላማ የቤተ ክርስቲያናችንን ድምፅ ይበልጥ ተደራሽ፣ ግልጽና ዘመናዊ ማድረግ ነው” ያሉት መምሪያ ኃላፊው፤ የሥልጠናው ተሳታፊዎች ከዚህ መድረክ የሚያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ቤተ ክርስቲያንን ከዘመኑ የሐሰት መረጃዎች የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመጨረሻም ለዚህ እጅግ ወሳኝ ሥልጠና መሳካት ሙሉ የገንዘብ ወጪውን በመሸፈን አጋርነቱን በተግባር ላሳየው ለአሐዱ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አባታዊ መልእክትና መመሪያ እንዲያስተላልፉ መድረኩን ጋብዘዋል።