በቡራዩ ከተማ የተገነባው “ፈለገ ጥበብ (ቡርቃ ኡጉማ)” አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ተመረቀ።
በቡራዩ፣ ገፈርሳ ጉጄ እና መልካ ኖኖ ክፍላተ ከተማ በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ሙሉ ወጪ የተገነባውና “ፈለገ ጥበብ (ቡርቃ ኡጉማ)” የተሰኘው አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በይፋ ተመርቋል ።በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ
አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተገኝተው ትምህርት ቤቱን መርቀዋል።
በተጨማሪም የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ዓለማየሁ ተፈራ፣ የቡራዩ ገፈርሳ ጉጄ እና መልካ ኖኖ ክፍላተ ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የቡራዩ ክፍለ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ
አቶ ዓሥራት አባተ እንዲሁም ሌሎች የሸገር ከተማ እና የቡራዩ ክፍለ ከተማ የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎች፣
አገልጋዮችና ምዕመናን በምረቃው ላይ ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና የተለያዩ የሥራ
ኃላፊዎች የገቡትን የገንዘብ ቃል ኪዳን ከሠራተኞችና ከምዕመናን ጋር በመተባበር ገቢ በማድረጋቸው ግንባታው በተሳካ ሁኔታ
ሊጠናቀቅ ችሏል። የከታ ወረዳ ነዋሪዎችና የትምህርት ማኅበረሰቡም ትምህርት ቤቱ ለአገር ተረካቢ ትውልድ መፍለቂያ ምንጭ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
ይህ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት የተገነባበት ዋነኛ ዓላማ በአገራችን የመንግሥት ዘመናዊ ትምህርት የሚጀምረው ከአንደኛ (1ኛ)
ክፍል በመሆኑና ቅድመ መደበኛ (መዋዕለ ሕፃናት) ትምህርት በከፍተኛ ክፍያ በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ ስለሚሰጥ የሚፈጠረውን
የትምህርት ተደራሽነት ልዩነት ለመቅረፍ እንደሆነ ተጠቅሷል። አቅም የሌላቸው ሕፃናት ያለ ቅድመ መደበኛ ዝግጅት አንደኛ (1ኛ)
ክፍል ሲገቡ ከሌሎች ጋር እኩል ለመራመድ የሚገጥማቸውን የአቅም ውስንነት ለመሙላት ትምህርት ቤቱ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው
ተገልጿል።
በምረቃው ወቅት ንግግር ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትን በየዛፉ ሥርና
በየአድባራቱ የጀመረች፣ ፊደል ቀርጻና ቀለም በጥብጣ በርካታ መጻሕፍትን የጻፈች መሆኗን አስታውሰዋል። ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ
ሕይወት ውስጥ የምታበረክተውን ሰላም የማውረድ ሥራና ታቦት ይዛ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እስከ ጦር ግንባር ድረስ ያደረገችውን ጉዞም ጠቅሰዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም “ትምህርት ቤት ዜጎች የሚቀረጹበት በመሆኑ ከሁሉ የላቀ ትልቅ ሥራ ነው” ካሉ በኋላ፣ ትምህርት ቤቱ
ሁሉንም በጋራ የሚያገለግልና ለሕዝብ ጥቅም የተሠራ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
አጠቃላይ ግንባታው በአምስት መቶ ዘጠና ሰባት ነጥብ ስምንት ስድስት (597.86) ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣
እያንዳንዳቸው ከአርባ እስከ አምሳ (40 እስከ 50) ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ክፍሎችን ይዟል። ትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ አሥራ ስድስት (16) ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፣ የሚከተሉትን ዝርዝሮች ያጠቃልላል።
1. ስምንት (
መማሪያ ክፍሎች
2. አንድ (1) የርዕሰ መምህር አስተዳደር ቢሮ
3. አንድ (1) የተማሪዎች መመገቢያ ክፍል
4. ሁለት (2) የሕፃናት ተማሪዎች ማረፊያ (መኝታ) ክፍሎች
5. አንድ (1) የጽዳት ዕቃ ማስቀመጫና ልብስ መቀየሪያ ክፍል
6. አንድ (1) የመምህራን ማረፊያና ጋዎን መቀየሪያ ክፍል
7. ሁለት (2) የመምህራን መጸዳጃ ክፍሎች በተጨማሪም አምስት በአምስት (5 በ 5) ሜትር የሆነ የመጸዳጃ ሴፍቲ ታንከር፣ ባለ ስድስት (6) ክፍል የተማሪዎች መጸዳጃ
ቤት፣ በሰማንያ (80) ቆርቆሮ የተሠራ የተማሪዎች ምግብ ማብሰያ ክፍልና ባለ አንድ (1) ክፍል የጥበቃ መኖሪያ ቤት ተገንብቶለታል።
ለግንባታው በጥሬ ገንዘብና በማቴሪያል በድምሩ ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ ሦስት መቶ አሥራ ስድስት ብር
ከሃምሳ ሳንቲም (6,586,316.50) የተገኘ ሲሆን፣ ለግንባታው ሥራ አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሰባት ሺህ አሥራ ሰባት ብር ከሃምሳ ሁለት ሳንቲም (5,537,017.52) ወጪ ተደርጓል።
በሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ የትምህርት ቤቱ ቁልፍ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አማካኝነት ለቡራዩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ለአቶ ፀጋዬ አመና የተላለፈ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚገልጽ ስያሜ ይሰጠው በሚለው ጥያቄ መሠረት፣ ቀደም ሲል “ቡኡራ ቦሩ” ተብሎ ይጠራ የነበረው ይህ ትምህርት ቤት በብፁዕነታቸው “ፈለገ ጥበብ አፀደ ሕፃናት (ቡርቃ ኡጉማ)” ተብሎ ተሰይሟል።
©Eotc tv