አዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተ በቋሚ ሲኖዶስ ከተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረሰ የተከሰቱትን ችግሮች ማለትም ሕገ- ወጥ ቅጥር፣ዕድገት ፣ዝውውር፣ሕገ- ወጥ የፋይናንስ አሰራሮችና የገንዘብ ዝውውሮች፣
ሕገ -ወጥ የቦታና የቤት ኪራይ ውሎችን ሕገ- ወጥ ተደራራቢ ሥራዎችን ወዘተ …በዝርዝር በማጥናት ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር የሚያቀርብ ኮሚቴ በመሰየም ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረጉ ይታወቃል።
በዚህም መሠረት የተቋቋመው ኮሚቴ የማጣራት ሥራው ውጤታማና ተቋም ተኮር፣እንዲሁም በሀቅ ላይ የተመሰረተና በሀገረ ስብከቱ የሚስተዋለውን ችግር ከመሠረቱ መፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሐሳብ የሚቀርብበት መሆን ይችል ዘንድ የቅድመ ማጣራት ስልቶችን በመቀየስ የማጣራት ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀዳሚ ዕቅዱ ከአካተታቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል መረጃዎችን የመሰብሰብ፣የመተንተንና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማደራጀት ሥራ ዋነኛ ተግባሩ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
በመሆኑም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተለይም ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከፍ ሲል በተዘረዘሩ ተግባራትና መሰል በሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ተጎጂ የሆናችሁና በቂ ማስረጃ ማቅረብ የምትችሉ ሁሉ ዘወትር በሥራ ሰዓት በእጃችሁ የሚገኘውን ማስረጃ ኮፒ በመያዝ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በተከፈተው የመረጃ መሰብሰቢያ ቢሮ በመገኘት በድምጽና በምስል ጭምር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በመስጠት የማጣራት ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችሉ መሆኑን እየገለጸ መረጃና ማስረጃ የሚሰጥ ማንኛውም አካል መረጃ በመስጠቱ ምክንያት በሥራው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስበት ኮሚቴው አስቀዶሞ በቋሚ ሲኖዶስ ዋስትና እንዲሰጥ ያደረገ መሆኑን እየገለጸ ያላችሁን መረጃና ማስረጃ በነጻነት ማቅረብ የምትችሉ መሆኑን ከወዲሁ ለማሳሰብ ይወዳል።
አጣሪ ኮሚቴው
ሐምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ