የገዳማት መምሪያ ለአህጉረ ስብከትና ገዳማት የሚያገለግሉ ልዩልዩ የቤተ ክርስቲያን መገልገያና የሶላር ኃይል ማመንጫ መሳሪያዎችን አበረከተ።
ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ- ኢትዮጵያበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት መምሪያ አስተባባሪነት ለተለያዩ አህጉረ ስብከትና ገዳማት አገልግሎት የሚውሉ ልዩልዩ ቁሳቁሶችና የሶላር ኃይል ማመንጫዎች ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ቢብዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ተበረከተ።
ስጦታውን ያበረከቱት የዋሽንግተን ዲሲ፣ ኦሪገንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሲሆኑ፣ እሳቸው ከሚያስተዳድሩት ሀገረ ስብከት ምዕመናንና የመንፈስ ወቅዱስ ልጆቻቸውን አስተባብረው በየጊዜው በሚላከው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በተለይም በገጠራማ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ገዳማትና አድባራት እንዲጠናከሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
በዚህም መሠረት ባለፈው ዓመት ለ36 ገዳማት የሶላር ኃይል ማመንጫዎች የተበረከቱ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ድጋፉ በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሎ ከ5 እስከ 6 ዓመታት የአገልግሎት ዋስትና (ጋራንቲ) ያላቸው 250 ትልልቅ የሶላር መሣሪያዎች ከነባትሪያቸው ለገዳማቱ እንዲደርሱ ተደርጓል።
ይህም በገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ ገዳማት የመንፈሳዊ አገልግሎት እንቅስቃሴ ትልቅ እፎይታ የሚያበረክት መልካም አጋጣሚ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት መምሪያ ኃላፊው መጋቤ ካህናት አባ ሀብተጊዮርጊስ አስራት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በተጣበበ የሥራ ሰዓታቸው ተገኝተው ፕሮግራሙን በማካፈላቸው ያላቸውን ደስታ የገለጹ ሲሆን አክለውም የቀረቡት ልዩልዩ ቁሳቁሶች በትክክል ለታለመላቸው መንፈሳዊ ዓላማ እንደሚውሉና የመምሪያው ሐዋርያዊ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።በተጨማሪም ይህ አሠራር መሥሪያ ቤቱን ካልተፈለገ ተጨማሪ ወጪ ያዳነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ለገዳማትና አድባራት አስፈላጊውን ድጋፍ ላደረጉት ለብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና ለገዳማት መምሪያው የላቀ ምስጋና በማቅረብ፣ አባታዊ መመሪያና ቡራኬ ሰጥተው መርሃ ግብሩ በሰላም ተጠናቋል።
ላዕከ ወንጌል ኃይሉ አየለ