“የብሔርና የዘረኝነት ፖለቲካ ወደ ቤተክርስቲያን ሰርጎ ሊገባ አይገባም” ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች ከተልእኳቸው ውጭ ወደሆነው
የፖለቲካና የብሔር መከፋፈል አጀንዳ ውስጥ ሊገቡ እንደማይገባ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አሳሰቡ።
የሸገር እና የደቡብ ምዕራብ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ይህንን የገለጹት፤ በዘንድሮው 45ኛው ዓለም አቀፍ (አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ) ጉባኤ ላይ መክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።
ቤተክርስቲያኒቱ እና ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በፈተና ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት ብፁዕነታቸው፣ በተለይም የብሔርና የዘረኝነት ፖለቲካ ወደ ቤተክርስቲያን ሰርጎ በመግባት መንጋውንም ሆነ አባቶችን እየፈተነ መሆኑን ተናግረዋል። “ቤተክርስቲያን የሁሉንም ቋንቋና ባህል እኩል የምታስተናግድ፣ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገች መንፈሳዊት ተቋም ናት እንጂ በጎሳ የምትከፋፈል አይደለችም”
ሲሉም በአጽንዖት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ መሆኑን ያወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ቤተክርስቲያኒቱ ለሀገር አንድነት፣ ለነፃነት፣ ለፊደል፣ ለትምህርት፣ ለስነ-ህንፃ፣ እና ለጥበብ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በቃላት የሚገለጽ አለመሆኑን አብራርተዋል።
አክለውም በዩኔስኮ ከተመዘገቡት የኢትዮጵያ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አብዛኞቹ የቤተክርስቲያኒቱ ሀብቶች መሆናቸውን እና ሀገር ስትወረር ታቦት ይዛ የዘመተች ታላቅ እናት መሆኗን አስታውሰዋል።
የዘንድሮው 45ኛው ጉባኤ ከቀደሙት ዓመታት ልዩ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው፣ ቀደም ሲል ጉባኤው በድንኳን ውስጥ ለዝናብና ለፀሐይ ተጋልጦ ይካሄድ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን ውብና ዘመናዊ በሆነ አዳራሽ ውስጥ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ዘመናዊ አዳራሽ ግንባታ መሳካት ትልቅ ሚና ለተጫወቱት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ለአዲስ አበባ
ከተማ ከንቲባ ክብርቲ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በቤተክርስቲያኒቱና በቅዱስ ሲኖዶስ ስም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም “ኃይላችን ያለው በመንፈሳዊነታችን፣ በፍቅራችን እና በአንድነታችን ውስጥ በመሆኑ ሁላችንም ወደ ልባችን ተመልሰን፣
ንስሐ ገብተንና ይቅር ተባብለን ለሀገራችን ሰላምና ለቤተክርስቲያናችን አንድነት ልንጸልይ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
እየተካሄደ ያለው 45ኛው ጉባኤም እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ፣ ተቋማዊ አሰራርን በማዘመን እና የቤተክርስቲያኒቱን ክብር ከፍ
በማድረግ ላይ አተኩሮ እንደሚመክር እምነታቸውን በመግለጽ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።©Eotc tv