በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አይሲቲና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።
ነሐሴ፳፯ ቀን፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ምአዲስአበባ -ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊት፤ ብሔራዊት፤ ዓለም አቀፋዊት፤ሐዋርያዊት እና ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆንዋ መጠን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፤ትውፊቷንና ሥርዓቷን በጠበቀ መልኩ መንፈሳዊ እና ማኀበራዊ አገልግሎቷን ለማጠናከር እና ተደራሽ ለማድረግ ከምታከናውናቸው በርካታ ተግባራት መካከል ዘመኑ የደረሰበት የአይሲቲና የዲጂታል ሽግግር ሥራ ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል::
ከዚሁ አንጻር የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን በመላው ዓለም ለማስፋፋት፣ ታሪካዊ ቅርሶችን እና አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረቷን ለመጠበቅ እንዲሁም አስተዳደራዊ ተግባራትን ለማሳለጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥራን በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ እንዲሁም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ተቃቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡
በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ ስምና ፊርማ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በተላከ ደብዳቤ፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ መቋቋሙን ገልጾ ቀደም ሲል እንደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያሉ አይሲቲን በዋና ክፍል አደራጅተው እየሠሩ የሚገኙ አህጉረ ስብከት በተላከላቸው ዝርዝር የሥራ መመሪያ ቁጥር 3/3018 መሠረት እስከ አጥቢያ ቤተ ከርስቲያን ጽ/ቤት ድረስ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲደረግ በተሰጠው መመሪያ መነሻነት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥራ ተጠናክሮ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ዶ/ር ዘሩ ብርሃኔ(ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዋና ክፍል ኃላፊ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ዘሩ ብርሃኔ(ቀሲስ) እንደገለጹት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ሰበሳቢ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ እና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ መጋቤ ጥበብ ሙሉዓለም አስራት በጋር በመሆን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለውን የጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ በአካል ተገኝተው የተመለከቱ ሲሆን በእርሳቸው አማካይነት ቀደም ሲል ስለተሠሩ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ሥራዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
በገለጻቸውም አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሥሩ ብዙ ሠራተኞች እና ሀብት የሚያስተዳድር ሀገረ ስብከት እንደመሆኑ ዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መጠቀም ዘመኑ የሚጠይቀው ሥራ ሆኖ በመገኘቱ ቀደም ሲል ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ክፍሉን በማደራጀት የሀገረ ስብከቱ ኦፊሻል ድረ-ገጽ www.eotcaa.org እና ሙሉ የሀገረ ስብከቱ ሕንፃ በኔትዎርክ በማገናኘት ፈጣን የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት የቻለ ሲሆን፣ የባለ ጉዳይ መመዝገቢያና መከታተያ ሲስተም www.aadapp.org በማበልጸግ እንዲሁም ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የመዝገብ ቤት እና ንብረት አስተዳዳር ሲስተም ተሰርተው የሀገረ ስብከቱ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዋና ክፍል እያስተዳደራቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በማስከተልም በማዕከል ደረጃ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አማካኝነት ስለተዘጋጁትና ተግባራዊ ስለተደረጉት ስትራቴጂ፣ ፖሊሲ እና መመሪያዎች እንዲሁም በለሙት የሰው ሀብት፤ የሰበካ ጉባኤ አስተዳዳር ሲስተም፣ ዌብ ፖርታል እና በመሳሰሉት የቴክኖሎጂ ሥራዎች በተመለከተ ከሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስከያጅ ከክቡር መልአከ ብርሃን ሰለሞን በቀለ ጋር በመገናኘት ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል የለሙት የሀገረ ስብከቱ መዝገብ ቤት እና ንብረት ሀብት አስተዳደር ሲስተሞች በክፍላተ ከተማ እና በገዳማትና አድባራት በማዕከል ደረጃ አገልግሎቱን ማግኘት ካለመቻላቸውም በላይ አሁን ላይ ቴክኖሎጂው ከደረሰበት አንፃር በእጅጉ ወደ ኋላ የቀሩ ሆነው በመገኘታቸው ሲስተሞቹ እንዲዘምኑ፤ እንዲሻሻሉ፣ ወቅታዊ እንዲሆኑ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በመልአከ ብርሃን ሰሎምን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ አማካኝነት ሥራው ለሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች የሥራ መመሪያ መስጠታቸው እና የባለ ጉዳይ መመዝገቢያና መመከታቲያ ሲስተም www.aadapp.org በተመለከተም በቂ ሥልጠና ተሰጥቶ ከመስከረም 2019 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ሥራው እንዲጀምር የሥራ መመሪያ መተላለፉን የሀገረ ስብከቱ የአይሲቲ ዋና ክፍል ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የአይሲቲ ዋና ክፍል ኃላፊው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የለሙ/የበለጸጉ ሲስተሞችን ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ሥራ ለማጀመር ሀገረ ስብከቱ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቅቆ እየጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ክፍሎችና የገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎች ከወዲሁ በቂ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር፣ የሰውና የቴክኖሎጂ ግብአት ዝግጅት እንዲያደርጉ እና ማንኛውም ከቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መዋቅሩን ጠብቆ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣቸው የአይሲቲ ፖሊሲና መመሪያዎች መሠረት ብቻ መከናወን እንዳለባቸው አውቀው ከዚህ ቀደም የለሙ እና ወደፊትም የታቀዱትን ሲስተሞች፣ ድረ ገጾች እና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ዝርዝር ለዋና ክፍሉ በደብዳቤ እንዲያሳውቁ አሳስበዋል።
ድረ-ገጽ፡ www.eotcaa.org
የባለ ጉዳይ መከታቲያ፡ www.aadapp.org