የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) መምሪያ የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን የሚያስችል የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ።
መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ
ከአይሲቲና ዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ጋር ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የሥልጠና የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ ።
በሥልጠው የአህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የአይሲቲ ዋና ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የተሳተፉ ሲሆን ፤ ሥልጠናው በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቁትን የአይሲቲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማስተዋወቅ፣ የሶፍትዌር ምንነት ለቤተክርስቲያኗ ዘመናዊ አሠራር ካለው ፋይዳ ጋር ማገናዘብ፣ እንዲሁም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና ዲጂታል ሚዲያ ቴክኖሎጂዎች በቤተክርስቲያኗ አገልግሎት ላይ የሚፈጥሯቸውን ዕድሎችና ተግዳሮቶች መመርመር ዋና ዓላማዎቹ አድርጓል።
በሥልጠና መዝጊያው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ መጋቤ ጥበብ ሙሉዓለም ዐሥራት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የኢንፎርሜሽን እና ኮሚንኬሽን የመምርያ ኃላፊ እና የድርጅት ኃላፊዎች ፣ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ የአማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ “ጥበብን ማግኘት ከወርቅ ይበልጣል” የሚለውን የመጽሐፍ ምሳሌ ኃሣብ በማንሳት ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘመኑን መዋጀ አገልግሎት እንድትሰጥ የኢፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ሥልጠና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሥልጠናው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ለቤተክርስቲያን አገልግሎት፦ በወቅታዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ በተደረጉ ውይይቶችም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለዘመናዊ የሰነድ አያያዝ፣ ለፈጣን መረጃ ልውውጥ እና ለሰፊ ተደራሽነት ትልቅ ዕድል መሆኑ ተነስቷል። አጠቃቀሙም ለወደፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ለሚጸድቁ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ግብአት እንደሚሆን ተመላክቷል።
በሥልጠናው መርሐ ግብር ላይ በተለያዩ ምሁራን የቀረቡ ጥናቶች እና ሙያዊ ማብራሪያዎች ቀርበዋል።
በሥልጠናዎቹ ዙሪያ ሙያዊ ውይይት ተከናውኗል ።
በሥልጠናው መጨረሻ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ በቀጣይ ትግበራ ላይ መመሪያ እና ኃሳብ ሰጥተዋል። የተግባር እቅድ ማውጣት፣ ያሉትን ክፍተቶች መሙላት፣ የመረጃ ጥራትን ማሻሻል፣ የአጠቃቀም መመሪያ ማውጣት፣ የደኅንነት ሥርዓት ማዘጋጀት፣ የሚድያ አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የAI ስህተቶችን ማረም ፣ ክትትል እና ግምገማ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሥልጠናውን ተከትሎ ሁሉም ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት የሰለጠነና ዘመናዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።
በድጅታል ሚድያ ቴክኖሎጂዎች ዙርያ የመነሻው ውይይቶች ተደርገው ለወደፊቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ለማጸድቁ ፖሊሲዎች እና መመሪያዎች ሃሳቦች እንደሚሰበሰቡም ታውቋል ።
በመጨረሻም ለሥልጠናው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና እና በብፁዕ ሥራ አስኪያጅ ቡራኬ በመስጠት፤ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል ።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/