የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ስለ ኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • መሠረታዊ መረጃዎች
      • ርእይ፣ ተልእኮ እና እሴቶች
      • ታሪክ
      • የአደባባይ በዓላት
      • ህግጋት
    • መዋቅር
      • ቅዱስ ሲኖዶስ
      • ሊቃነ ጳጳሳት
      • መምሪያዎች
      • አህጉረ ስብከት
      • ትምህርት ቤቶች
  • አስተምህሮ
    • አእማደ ምሥጢር
      • ምሥጢረ ሥላሴ
      • ምሥጢረ ስጋዌ
      • ምሥጢረ ጥምቀት
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ትንሳኤ ሙታን
    • ምሥጢራተ ቤተክርስትያን
      • ምሥጢር ጥምቀት
      • ምሥጢረ ሜሮን
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ንስሐ
      • ምሥጢረ ተክሊል
      • ምሥጢረ ክህነት
      • ምሥጢረ ቀንዲል
    • ልዩ ልዩ
      • ነገረ ድኅነት
      • ነገረ ማርያም
      • ነገረ ቅዱሳን
      • ነገረ መስቀል
      • ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው
  • አገልግሎቶች
    • ሐዋርያዊ ተልእኮ
    • ማኅበራዊ አገልግሎት
    • የልማት እንቅስቃሴዎች
    • ምግባረ ሰናይ
  • መካናት
    • ቅዱሳት መካናት
      • አክሱም ጽዮን
      • ላሊበላ
      • ደብረ ሊባኖስ
      • ማውጫ
    • ቤተ መዛክርት
      • መንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ቤተ መዘክር
      • የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገስት በአታ ለማርያም ቤተ መዘክር
      • ማውጫ
    • የጉብኝት መረጃዎች
      • የጉዞ መረጃዎች
      • የሚጠበቅ ሥርዓት
  • ያግኙን
  • English Site
  • Menu Menu

የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የ፳፩ኛ ዓመት በዓለ ሢመት

August 29, 2026
የዛሬ ፳፩ ዓመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ነሐሴ ፳፪ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተካሄደው ሥርዐተ ሢመት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ፲፯ አባቶች ተሹመዋል፡፡
ከእነዚህ አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ድርጅት እና የምሥራቅ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም መሠረት ሦስቱን ብፁዓን አባቶቻችንን በጥቂቱ እናስታውሳቸው፡፡ /ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ መስከረም 1998 ዓ.ም/፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በ፲፱፻፺፯ ዓም በተደረገ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ከሌሎች ፲፮ ብፁዓን አባቶች ጋር በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት አንብሮተ እድ ተሹመው በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በኬንያ፣ በሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነት አገልግለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በ፳፻፰ ዓ.ም በተካሄደው የግንቦት ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከሌሎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት በእጩነት ቀርበው በከፍተኛ ድምፅ በማለፋቸው ከ፳፻፰ እስከ ፳፻፲፩ ዓ.ም ግንቦት ወር ድረስ ለሦስት ዓመታት በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት በትጋትና በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በዘመነ ሢመታቸው በአህጉረ ስብከትም ሆነ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት የሥራ ዘመናቸው ለቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተልዕኮ መሳካት፣ ልዕልናና እድገት በመሥራት ያስመዘገቧቸው ውጤቶን እጅግ የሚደነቁ ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት የሥራ ዘመናቸው የቤተክርስቲያን ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተከብረው ሥራዎች እንዲሠሩ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል፡፡ በተለይም የቤተክርስቲያን ልዕልናና ክብር እንዲጠበቅ የሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ በሕግና በመመሪያ እንዲፈጸሙ፣ ከዚህ በተጨማሪም በተመደቡበት በደቡብ ምዕራብ ሸዋና በሸገር አህጉረ ስብከት በሰላም፣ በፍቅርና በስምምነት ሥራዎቻቸውን በመፈጸም፣ የካህናትና የአገልጋዮች መብት እንዲከበር፣ መንፈሳዊ አገልግሎቶቸው ሁሉ በፍቅርና በስምምነት በማከናወን በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ በማድረግ በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ከአንጋፋና ዘመን ከአስቆጠሩ ብዙ አህጉረ ስብከቶች የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገቡ ለመሸለምና ለመመስገን የበቃ ሀገረ ስብከትን ፈጥረዋል፡፡ የሸገር ሀገረ ስብከት ከሌሎች አህጉረ ስብከቶች በተሻለ መልኩ የመልካም አስተዳደር ሥርዐት የሚታይበት ነው፡፡ /ልማት በቤተክርስቲያን መጽሔት፤ ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም/፡፡
ብፁዕነታቸው ሌላው የሚታወቁበት በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ነው፡፡ በሀገረ ስብከቱ “ወጣትነት ለቤተክርስቲያን” በሚል ርእስ በሸገርና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ላይ በስፋት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በሸገር ከተማና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ደረጃ በብፁዕነታቸው አመራር ሰጪነት የተቋቋመው ወጣትነት ለቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት በአጠቃላይ በስብከተ ወንጌል ዘርፍ ስኬታማ ሥራዎች ለመሥራት ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅትን አሠራር ማዘመን ይቻል ዘንድ ብፁዕነታቸው የሰጡትን አመራር የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ዘመናዊና ዲጃታል እንዲደረግ፣ድርጅቱ የራሱ የሆነ ድረ ገጽ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ በትንሣኤ አሳታሚ ድርጅት ከፍተኛ ወጪ ታትመው የተከማቹ መጻሕፍቶችን በማሰራጨት ሥራ መላውን የቤተክህነት ሠራተኛን በማሳተፍ መጻሕፍቶቹ በጨረታ ተሸጠው የቤተክርስቲያን ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ፣መጻሕፍቱም አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ታሪኮቿ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን፣ልዩልዩ ሃብቶቿን፣ የያዙ የታሪክ ሰነዶች ተለይተው፣ተደራጅተውና በዘመናዊ መልኩ ወደ ዲጂታል ፋይል ተቀይረው ለታሪክና ለትውልድ እንዲተላለፉ እየተከናወነ ይገኛል።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ቅጽር ጊቢ በሚገባ ጸድቶ፣አምሮና ተውቦ፣ለዕይታ የሚማርክ፣የቤተክርስቲያንን ክብር የሚመጥን፣ ቅጽረ ጊቢ እንዲሆን ተደርጓል። አሮጌው ቄራ በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ በመሠራት ላይ የነበሩት ሁለት ግዙፋን ሁለገብ ሕንጻዎችም ትኩረት ሰጥቶ ለውጤት አብቅተዋል፡፡አሁንም ቤተክርስቲያን በመጪው ዘመን መንፈሳዊ አገልግሎቷን የምትጠቀምበት ዘመናዊ ሕንጻዎች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዘመነ ሢመታቸው ከሠሯቸው በርካታና ውጤታማ ሥራዎች መካከል በታሪክ መዝገብ ከሚሰፍሩ ሥራዎቻቸው መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው የሸገር ሀገረ ስብከት ውጤታማ ሥራቸውና ከአስተዳደራዊ ሥራዎች በተጓዳኝ የሚያከናውኗቸው የመንፈሳዊ አገልግሎቶች ናቸው። ብፁዕነታቸው በሚገርም ትጋትና ብቃት የአስተዳደራዊና የልማት ሥራዎችን ከመምራት በተጓዳኝ በዓበይት በዓላት፣በአብያተ ክርስቲያናት ምረቃ፣በስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች፣ወዘተ በሀገረ ስብከታቸው በየጊዜው በመገኘት ወጣቱ ትውልድ በስብከተ ወንጌል አማካኝነት፣በቃለ እግዚአብሔር ታንጾ እንዲያድግና የቤተክርስቲያን ተረካቢ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እያደረጉት ያለው ጥረትና እያስመዘገቡት ውጤት የመሪነት ብቃታቸውን የሚያሳይ ነው።
ብፁዕነታቸው በልማትም ይታወቃሉ፤ በሀገረ ስብከቱ ያለ መሰልቸት ትልቅ ትንሽ ደብር ነው፣ ገጠር ነው ከተማ ሳይሉ በአስቸጋሪ ቦታና ሁኔታ ሳይቀር አልፈው ሐዋርያዊ አገልግሎት ይጓዛሉ፡፡ በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ሁሉ ሳይቀር ለተሠሩ ሥራዎችና ልማቶች ምስጋና አቅርበው ወደፊትም ለሚሠሩት አቅጣጫ ሰጥተው የሚመለሱ የልማት አባት ሠርተው የሚያሠሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በ፲፱፻፺፯ ዓ.ም በተደረገ ሢመተ ጳጰሳት ከሌሎች ፲፮ ብፁዓን ኤጲስ ቆጶሳት ጋር ተሹመው በደቡብ ትግራይ ማይጨው፣ በደቡብ ምሥራቅና በአዲግራት አህጉረ ስብከት በሊቀ ጳጳስነት እንዲሁም ከ፳፻፮-፳፻፱ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት በዋና ሥራ አስኪጅነት በትጋት በጥንካሬ በታማኝነትና በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በአህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነትም ሆነ በጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸው ለቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተልዕኮ መሳካት፣ ልዕልናና ዕድገት የሠሯቸው ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው ስብከተ ወንጌል በማስፋፋት፣ በልማት ተተኪ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ወዘተ…ያከናወኗቸው ተግባራት ሰፊ ናቸው፡፡ ሕገ ቤተክርስቲያን፣ ቃለ ዓዋዲና ሌሎች ሕጎችና ደንቦችን አክበረው የሚያስከብሩ ሥራዎቻቸው ሁሉ በዕውቀት፣ በአባትነት መንፈስና በተቋማዊ ተቆርቋሪነት የሚመሩ እጅግ የተዋጣላቸው አባት ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ብፁዕነታቸው በተለይም በሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸው ያላቸውን ከፍተኛ የአመራር ብቃት በመጠቀም ለቤተክርስቲያን |ዕድገትና ልዕልና ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ያስመዘገቡት ተቋማዊ ዕድገት ከፍተኛ ዕውቅና እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ /ዝኒ ከማሁ/፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በበላይ ሊቀ ጳጳስነት እንዲመሩት የሰጣቸውን የቅርስ ጥበቃ፣ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያን በሰው ኃየይልና በቁሳቁስ ተደራጅቶ እንዲሠራ ለማድረግ ካደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በተጨማሪ የቤተክርስቲያን አእምሮአዊ ንብረቶች እንዲጠበቁና በአእምሮአዊ መብትነት እንዲመዘገቡ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ ኮሚቴ በመሰየምና ኮሚቴውን በአግባቡ በመመራት የቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት በአእምሮአዊ ንብረት እንዲመዘገብ አድርገዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሥራዎቻቸው ሀሉ ቅድሚያ ለቤተክርስቲያን ተቋማዊ ህልውና የሚሰጡ ትጉህ አባት ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ በግንቦት ፳፻፲፯ ዓ.ም የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በማድረግ መርጣቸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በከፍተኛ ድምጽ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ደረጃውን በጠበቀና የቅዱስ ሲኖዶስን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲደራጅ ፣ እንዲዋብ በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ያማረና ግሩም እንዲሆን አድርገውታል። የቅዱስ ሲኖዶስን ሥራ የሚያግዙ ምሁራን የሥራ ኃላፊዎችን በማሳተፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ በአግባቡ እንዲጻፍ፣የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲዘጋጅና ወጥነት ያለው የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓት በማድረግ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ችለዋል። ለዚህ ውጤታማነታቸው ትልቁ ምክንያትም ብፁዕነታቸው ያላቸው የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ፣ብልሃት የተሞላበት የመሪነት ክህሎት፣አርቆ የማሰብ ብቃት፣መጠነ ሰፊ ተቋማዊ አመለካከት፣ ለቤተክርስቲያን ሉዓላዊነት እና ክብር በቆራጥነት የመሥራት የዳበረ ልምድና ፍጹም የሆነ የሁለንተናዊ ብቃት ባለቤት መሆናቸው እንደሆነ የሚጠራጠር አይደለም።/ዝኒ ከማሁ/፡፡
ብፁዕነታቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች እንዲተገበሩ፣ ዘመኑን በመዋጀት ቤተክርስቲያንን እንዲያስከብሩ፣ በአጠቃላይ የቤተክርስቲያንን ሁለንተናዊ ጥቅሞች ተቋማዊ በሆነ መልኩ ያስከበሩ አባት ናቸው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤትን በአግባቡ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ማደራጀት ለቤተክርስቲያን እድገትና ልዕልና መከበር የሚረዱ ጥናቶች እንዲጠኑና በተግባር እንዲውሉ በማድረግ ቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ክብሯን ለቀጣዩ ትውልድ እንድትላለፍ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
በአጠቃላይ ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር በመናበብና በመተባበር ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት ጠንክረው በመሥራት ቤተክርስቲያን በ21ኛው መ/ክ/ዘ የሚጠበቅባትን ሥራ እንድታከናውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በቤተክህነት ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በ፲፱፻፺፯ ዓም በተደረገ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ከሌሎች ፲፮ ብፁዓን አባቶች ጋር በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት አንብሮተ እድ ተሹመው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነት አገልግለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በዋግህምራ፣ በሶማሌ ጅግጅጋ፣ በወላይታ አህጉረ ስብከት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ድርጅት የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ብፁዕነታቸው የቤተክርስቲያናችን ቁልፍ ሥራ የሆነውን የስብከተ ወንጌል መስፋፋትና መጠናከርን ዕውን ለማድረግ ሚዲያውን በማጠናከር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበበትም ወቅት ነው፡፡
ድርጅቱ በተለይም ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ በሰው ኃይልና በመርሐ ግብር ዝግጅት ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ይገኛል፡፡ በተለይም የቤተክርስቲያናችን ተቋማት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን የፕሮግራም ይዘቶች መሻሻል፣ የዜናና የፕሮግራም አቀራረቦች ዘመኑን የሚመጥኑ እንዲሆኑ መደረጉ፣ ዜናዎች በመልክና በይዘታቸው ተለይተው እንዲሰራጩ መደረጉ፣ ወቅታዊ ፕሮግራሞች ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲለቀቁ መደረጉ፣ የቀጥታ ሥርጭቶችና አስፈላጊ መረጃዎች በፍጥነት እንዲሰራጩ በማድረግ የብፁዕነታቸው አመራር ውስጥ በስኬት ካከናወናቸው በርካታ ውጤቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
እነዚህ ስኬቶች ሊመዘገቡ የቻሉትም የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመርሐ ግብር አዘጋጆችና ጋዜጠኞች ተናበውና ዕቅድ አውጥተው በመሥራታቸው እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ለለውጡ፣ለዕድገቱ መመዝገብ ትልቁ ድርሻ የብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ይሆናል።
እንደ ማጠቃለያ
በጽሑፉ መግቢያ እንደገለጽኩት በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የሞከርኩት የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት 21ኛ ዓመት በዓለ ሢመት፣ የተሠሩ ሥራዎችን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከሁለቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተጨማሪ በዚሁ ዕለት የተሾሙት
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣
ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣
ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፣
ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣
ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፣
ብፁዕ አቡነ ሔኖክ፣
ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፣
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣
ብፁዕ አቡነ ሰላማ፣
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፣
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣
ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ እና
ብፁዕ አቡነ ኤውስጣቴዎስ ናቸው፡፡
የብፁዓን አባቶቻችን ቡራኬያችሁ ይድረሰን !!!
ዋቢ መጻሕፍት
✍️ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፤ መስከረም 1998 ዓ.ም
✍️ ልማት በቤተክርስቲያን ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም
✍️ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ድረ ገጽ
Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/pr000077.jpeg 336 336 eotceth https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/eotceth-logo2.svg eotceth2026-08-29 04:22:252026-08-29 04:22:25የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የ፳፩ኛ ዓመት በዓለ ሢመት
Search Search

Recent Posts

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት መጪውን በዓል ምክንያት በማድረግ ለቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ መሪዎች «የእንኳን አደረሳችሁ» ስጦታ አበረከተ።
  • የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ላለፉት ሁለት ዓመታት ያሰተማራቸውን ደቀ መዛሙርት አስመረቀ !!!
  • ጳጉሜ የሚለው ስያሜ ‹‹ኤፓጉሜኔ›› ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ጭማሪ›› ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭)
  • የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች ለተባባሪ ፕሮፌሰር ለብፁዕ አቡነ ፊልጶስ(ዶ/ር) የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመመረቃቸው ልዩ የደስታና የምስጋና መርሐ ግብር አካሄዱ።
  • “መስከረም በአታ የሃያ ሺህ ሰዎች ምሥረታ” በሚል የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የአብነት ትምህርት ቤት ሕንጻ ግንባታ ድጋፍ ማስጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በተገኙበት ተሰጠ።

Archives

  • September 2026
  • August 2026
  • July 2026
  • June 2026
  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • January 2026
  • December 2025
  • August 2025
  • July 2025
  • June 2025
  • March 2025
  • February 2025
  • January 2025
  • December 2024
  • November 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • July 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • April 2024
  • March 2024
  • February 2024
  • January 2024
  • December 2023
  • November 2023
  • October 2023
  • September 2023
  • August 2023
  • July 2023
  • June 2023
  • May 2023
  • April 2023
  • March 2023
  • February 2023
  • January 2023
  • December 2022
  • October 2022
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church
  • Link to Facebook
Link to: የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ክፍት የሥራ ማስታወቂያ Link to: የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ክፍት የሥራ ማስታወቂያ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት... Link to: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአይሲቲና የዲጂታል ሽግግር መዋቅር እየተተገበረ መሆኑ ተገለጸ:: Link to: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአይሲቲና የዲጂታል ሽግግር መዋቅር እየተተገበረ መሆኑ ተገለጸ:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top