የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአይሲቲና የዲጂታል ሽግግር መዋቅር እየተተገበረ መሆኑ ተገለጸ::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማዋን ቀኖናዋንና ሥርዓቷን በጠበቀ መልኩ መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለማጠናከር ከምታከናውናቸው በርካታ ተግባራት መካከል ዘመኑ የደረሰበት የአይሲቲና የዲጂታል ሽግግር ሥራ ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል:: ይህንንም ሥራ በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የተቋቋመው የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ወደ ሥራ መግባቱ ታውቋል።
የግንቦት 2018 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ መሪነት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በዓመቱ ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ተግባራትን በመመልከት ቤተክርስቲያን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትሆን መመሪያ ማስተላለፉ ይታወሳል።
በዚህ መሠረት ለበርካታ ወራት በሙያው የተሰማሩ በጎፈቃደኛ አገልጋዮች ዝግጅት ሲደረግባቸው የቆዩ የአይሲቲ ፖሊሲ ፣ የአይሲቲ መምሪያ ማቋቋሚያ ደንብ ፣ የአይሲቲ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እና የአይሲቲና የዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ የሥራ መመሪያ በቅዱስ ሲኖዶስ ታይተውና ጸድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ እየተደረጉ መሆናቸውን መጋቤ ጥበብ ሙሉዓለም ዐሥራት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሓላፊ ገልጸዋል።
አዲስ ለተቋቋመው የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ግልጽ የሥራ ማስታወቂያ የወጣ መሆኑን የገለጹት ሓላፊው ሌሎች አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ግብአቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪጅ ስምና ፊርማ በውስጥና በውጭ ለሚገኙ አህጉረ ስብከት በዲጂታል መገናኛ ዘዴዎች በተላከ ደብዳቤ ፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ በመቋቋሙ በየሀገረ ስብከቱ ደግሞ የአይሲቲ ዋና ክፍል እንዲደራጅና በሥር ባሉ ወረዳዎችና አጥቢያዎች እንደአስፈላጊነቱ እንዲቋቋሙ መመሪያ መውረዱን መጋቤ ጥበብ ሙሉዓለም ዐሥራት አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ቀደም ብለው አይሲቲ ክፍልን በዋና ክፍል አደራጅተው እየሠሩ የሚገኙ አህጉረ ስብከት በተላከላቸው ፖሊሲና መመሪያ መሠረት መዋቅሩን አጠናክረው ከመምሪያው ጋር በመተባበር ሥራቸውን መቀጠል እንደሚኖርባቸውም ተገልጿል።
በተለይም በቅርቡ ሥራ ላይ ይውላሉ ተብለው የሚጠበቁት ልዮ ልዮ ሲስተሞችን ተግባራዊ ለማድረግ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት አማካይነት በጠቅላይ ቤተክህነት ለሚገኙ መምሪያዎችና ድርጅቶች እንዲሁም ለሁሉም አህጉረ ስብከት በተጻፈ ደብዳቤ የተላለፉ ዝርዝር ተግባራትን በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ የገለጹት ሓላፊው በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ያሉና በየጊዜው የሚከናወኑ ከኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማቶች ጋር የተያያዙ ማናቸውም ዓይነት ተግባራት ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣቸው የአይሲቲ ፖሊሲና መመሪያዎች መሠረት ብቻ መከናወን እንደሚኖርባቸው መመሪያ መተላለፋን ጠቁመዋል።