የወሊሶ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ቡኡራ ቦሩ አጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተመረቀ።
ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኘው የወሊሶ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት የተገነባው የቡኡራ ቦሩ አጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በጸሎተ ተባርኮ በይፋ ተመረቀ።
የቡኡራ ቦሩ አጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም. የተመረቀ ሲሆን፣ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ የሸገር ከተማ እና የምስካየ ሕዙናን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ እንዲሁም መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የለገጣፎ ለገዳዲ፣ የኩራ ጂዳ፣ የቡራዩ ገፈርሳ እና የጉጄ መልካ ኖኖ ክፍላተ ከተማዎች ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በተጨማሪም የወሊሶ ከተማ ከንቲባ አቶ ገመቺስ አረዳ፣ የአካባቢው የጸጥታ አካላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸውንና ተጋባዦችን መርሐ ግብሩ በሚካሔድበት ሥፍራ ሲደርሱ የወሊሶ ከተማ ከንቲባ አቶ ገመቺስ አረዳ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ፍቅረ ሥላሴ እንዲሁም የአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች በጋራ በመሆን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ይህ አዲስ የትምህርት ቤት ሕንፃ ከሀገር ውጭና በወሊሶ ከተማ በሚገኙ ምዕመናን አማካኝነት ግንባታው መካሄዱ ተገልጿል። ሕንፃው ሰባት የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ለሕፃናት የትምህርት እና የእውቀት መስፋፊያ እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ መልካም መሠረት ለመጣል የሚያገለግል መሆኑ ተገልጿል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፣ “ሕፃናት በዚህ ትምህርት ቤት ተምረው ቤተ ክርስቲያናቸውንና አገራቸውን ማገልገል እንዲችሉ የተሠራው ሥራ እጅግ መልካም ነው” ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም፣ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሕክምና ተቋም፣ የማኅበረሰብ አስታራቂ ሽማግሌዎችና ካህናት መገኛ መሆኗን አስታውሰው፣ ለነገዋ አገር ተረካቢ የሆነ ትውልድ ማግኘት እንዲቻል እንዲህ ያሉ የትምህርትና የልማት ሥራዎች ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
“ትምህርት ቤት የሁሉም ሰው መገልገያ በመሆኑ ይህ የልማት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ሊስፋፋ ይገባል፤ የታሪክ አሻራችሁም መልካም ነው” ሲሉ ለተሳተፉትና ለዚህ ሥራ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምስጋና አቅርበዋል።
የወሊሶ ከተማ ከንቲባ አቶ ገመቺስ አረዳ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ “ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም የሰላምና የፍቅር ምንጭ ናት” ካሉ በኋላ፣ በተለይም ማኅበራዊ ኃላፊነቷን በመወጣትና እንዲህ ያሉ የልማት ሥራዎችን በመገንባት ረገድ የምታበረክተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው የከተማ አስተዳደሩም ለትምህርት ቤቱና ለተያያዙ የልማት ሥራዎች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም በትምህርት ቤቱ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላት እውቅና የተሰጠ ሲሆን በሥራ አፈጻጸማቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የሥራ ኃላፊዎችም የማዕረግ ስም ተሰጥቷቸዋል።ሲል የሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል በላከልን ዘገባ ገልጿል።