የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ስለ ኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • መሠረታዊ መረጃዎች
      • ርእይ፣ ተልእኮ እና እሴቶች
      • ታሪክ
      • የአደባባይ በዓላት
      • ህግጋት
    • መዋቅር
      • ቅዱስ ሲኖዶስ
      • ሊቃነ ጳጳሳት
      • መምሪያዎች
      • አህጉረ ስብከት
      • ትምህርት ቤቶች
  • አስተምህሮ
    • አእማደ ምሥጢር
      • ምሥጢረ ሥላሴ
      • ምሥጢረ ስጋዌ
      • ምሥጢረ ጥምቀት
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ትንሳኤ ሙታን
    • ምሥጢራተ ቤተክርስትያን
      • ምሥጢር ጥምቀት
      • ምሥጢረ ሜሮን
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ንስሐ
      • ምሥጢረ ተክሊል
      • ምሥጢረ ክህነት
      • ምሥጢረ ቀንዲል
    • ልዩ ልዩ
      • ነገረ ድኅነት
      • ነገረ ማርያም
      • ነገረ ቅዱሳን
      • ነገረ መስቀል
      • ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው
  • አገልግሎቶች
    • ሐዋርያዊ ተልእኮ
    • ማኅበራዊ አገልግሎት
    • የልማት እንቅስቃሴዎች
    • ምግባረ ሰናይ
  • መካናት
    • ቅዱሳት መካናት
      • አክሱም ጽዮን
      • ላሊበላ
      • ደብረ ሊባኖስ
      • ማውጫ
    • ቤተ መዛክርት
      • መንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ቤተ መዘክር
      • የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገስት በአታ ለማርያም ቤተ መዘክር
      • ማውጫ
    • የጉብኝት መረጃዎች
      • የጉዞ መረጃዎች
      • የሚጠበቅ ሥርዓት
  • ያግኙን
  • English Site
  • Menu Menu

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም የ76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት እና በጀግኖች አባቶቻችን ለተገኘው 85ኛው የኢትዮጵያ የድል በዓል ያስተላለፉት መልዕክት

May 5, 2026

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን — በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን — አግአዞ ለአዳም
ሰላም — እምይእዜሰ
ኮነ — ፍሥሐ ወሰላም
​”ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር”
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ” መዝ. 68፡31
• ​ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤
• ​የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመመሪያ ኃላፊዎች፤
• ​የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የመመሪያ ኃላፊዎች፤
• ​ክቡራን የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ አባላት፤
• ​የገዳማት እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፤
• ​ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና የገዳሙ አበው መነኮሳት አኃው ዲያቆናት እንዲሁም የገዳሙ ተቋማት ልዩ ልዩ ሠራተኞች፤
• ​የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፤
• ​ከሩቅም ከቅርብም የመጣችሁ የመድኃኔዓለም ወዳጆች ምዕመናንና ምዕመናት፤
• ​እንዲሁም ሕፃናት በቅድሚያ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ።
​በድጋሚ ዛሬ ለምናከብረው ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም የ76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት እና በጀግኖች አባቶቻችን ለተገኘው 85ኛው የኢትዮጵያ የድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ።
• ​ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
• ​ክቡራንና ክቡራት የበዓሉ ተካፋዮች
​በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓል ሁለት መልክ ያለው ድርብ በዓል ነው።
​አንደኛው በዚህ ታላቅ ገዳም የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኔ ዓለምን ታቦተ ሕግ ከመንበረ ክብሩ አውጥተን ቅዳሴ ቤቱን በማሰብ የምናከብረው በዓል ሲሆን፤
​ሁለተኛው በኢትዮጵያውያን ካህናት፣ ምዕመናን እና በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ጸሎት እንዲሁም በኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎ የተገኘው የድል በዓል ነው።
​ይህ የኢትዮጵያውያን ድል ይገኝ ዘንድ ጀግኖች አባቶቻችንን የረዳ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦተ ሕግ በመሆኑ ስለ ታቦተ ሕጉ እንዲሁም ስለ ገዳሙ ጥቂት ለማለት እንወዳለን።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦተ ሕግ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና በንግሥት ጣይቱ መልካም ፈቃድ በመምህር ፈቃደ እግዚአ እንቁላላዊ አማካኝነት በ1895 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ከዚያም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ላሉ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን በዴር ሱልጣን ገዳም አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
​የመድኃኔ ዓለም ታቦት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት በ1895 ዓ.ም ሲሆን ታቦተ ሕጉ እስከ ዛሬ ድረስ የምዕመናን…
​ልመናና ጸሎት በመስማት፣ ያዘኑትን በማጽናናት፣ የተቸገሩትን በመርዳት መጠጊያ ለሌላቸው መጠጊያ በመሆን ለ123 ዓመታት አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦተ ሕግ ከ1895 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት የተለያዩ ሀገሮች ላይ አገልግሎት ሰጥቷል።
​1ኛ. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለ34 ዓመታት ከኢትዮጵያውያን ምዕመናን ጋር፤
2ኛ. በእንግሊዝ ሀገር ለ4 ዓመታት ከጃንሆይ ጋር፤
3ኛ. በኢትዮጵያ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞ ስሙ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በአባ ኃይለ ማርያም እየታጠነ ለ2 ዓመታት፤ እንዲሁም የካቲት 12 ሆስፒታል በቀድሞ ስሙ ቤተ ሳይዳ ለ7 ዓመታት።
​አሁን ባለንበት የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለ76 ዓመታት፣ በአጠቃላይ እስከ ዛሬ ድረስ 123 ዓመታት ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም የሄደበት ዓላማ በዚያ ላሉ ምዕመናን መድኃኔ ዓለምን መማጸኛና መንፈሳዊ አገልግሎትን ማከናወኛ ይሆን ዘንድ ነበር።
​ነገር ግን ወራሪው ጠላት ፋሽስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ተኝቶ ለመግዛት ወረራን ፈጽሞ በነበረበት ወቅት ግርማዊ ጃንሆይ ለተባበሩት መንግሥታት አቤቱታቸውን ለማሰማት ወደ እንግሊዝ ሀገር ተሰደዱ።
​እንግሊዝ ሀገር በስደት በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ጉዳይ በምድራዊ ዳኞች ፍትሕ ሊያገኝ ስላልቻለ ጥር 13 ቀን 1929 ዓ.ም ግርማዊነታቸው በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ በመጨረሻ የሚመራ ስማቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩ፦
​ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ
​ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
​ይድረስ ለብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ነገር እስከሚያሳየን ድረስ በዚህ ስለምንቆይ ቤተሰቦቻችንም ሃይማኖታቸውን እንዳይዘነጉ አምላካችንን የምንማጸንበት ታቦት ያስፈልገናል።
​ስለዚህ አባ ሐናን መልዕክተኛ አድርገን ስለላክን ከመምህር ገሪማ ጋር ተነጋግራችሁ አንድ ታቦት እና ንዋያተ ቅዱሳት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከውሉን አገልጋዮች ጋር ላኩልን በማለት መልዕክታቸውን አደረሱ።
​መልዕክቱን የተቀበሉት ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ በወቅቱ የአገልጋይ እጥረት እንዳለ ገልጸው የመድኃኔ ዓለም ታቦትንና ንዋያተ ቅዱሳቱን በማሟላት ከአራት አገልጋይ መነኮሳት ጋር መልዕክተኛው አባ ሐናን መሪ በማድረግ ወደ እንግሊዝ ሸኝተዋል።
​ግርማዊ ጃንሆይም ከኢየሩሳሌም የመጣላቸውን የመድኃኔ ዓለም ታቦት የእንግሊዝ መንግሥት በሰጣቸው ባት በሚባል የአምልኮ ስፍራ ሚያዝያ 27 ቀን 1929 ዓ.ም ከኢየሩሳሌም በመጡት መነኮሳት እና በአባ ሐና አማካኝነት ከመላው ቤተሰባቸው ጋር ለሀገራቸው እና ስለ ኢትዮጵያውያን ሱባኤ ይዘው መድኃኔ ዓለምን መማጸን ጀመሩ።
​በወቅቱ ከሚጸልዩት ጸሎት መካከልም፦
​ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8፥35 በጻፈው መልዕክት የሚገኘውን ኃይለ ቃል በመጠቀም ነበር።
​ቃሉም፦
​”ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይንስ ስደት ወይንስ ራብ ወይንስ ዕራቁትነት ወይንስ ፍርሃት ወይንስ ሰይፍ ነው?” የሚል ሲሆን
​ከሚዘምሩት መዝሙሮች መካከልም፦
“ኢትዮጵያ ሆይ በረከሸ ቀኝ ትርሳኝ” የሚል ይገኝበታል።
​ይህ ኃይለ ቃልና መዝሙር እስከ ዛሬ ድረስ በገዳሙ የሰርክ ጸሎት እየተጸለየ ይገኛል።
​ከ4 ዓመታት በኋላም በ1933 ዓ.ም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የግርማዊነታቸው እና የኢትዮጵያውያን ጸሎት ተሰምቶ በመድኃኔ ዓለም ተራዳኢነት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ጣሊያንን ድል አደረጉ።
​በዚህ ጊዜ ግርማዊነታቸው “መድኃኔ ዓለም ጸሎታችንን ሰምቶናል፣ በጠላቶቻችን ላይ ድል እንድንቀዳጅ አድርጎናል” አሉ።
​ስለዚህ ጸሎት እና ልመናችንን የሰማን የመድኃኔ ዓለምን ታቦት ይዘን ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መሄድ አለብን በማለት የመድኃኔ ዓለምን ታቦት እና ንዋያተ ቅዱሳት እንዲሁም አገልጋይ መነኮሳትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ላይ አድርገው በ1933 ሚያዝያ 27 ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
​በዚህ ዕለትም ግርማዊነታቸው ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በአዲስ አበባ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለው በመውለብለብ የድል በዓሉን አክብረዋል።
​ይህ የድል በዓል ዘንድሮ ለ85ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት ከአገር ወደ አገር ሲንቀሳቀስ ያረፈባቸው ቦታዎች 5 ናቸው።
​እነሱም፦
• ​ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም
• ​ከኢየሩሳሌም ወደ እንግሊዝ
• ​ከእንግሊዝ ወደ ካርቱም
• ​ከካርቱም ወደ አሜድላ
• ​ከአሜድላ ወደ አዲስ አበባ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት በሦስት ስሞች ይጠራል።
​1ኛ. ዴር ሱልጣን መድኃኔ ዓለም፦ ዴር ሱልጣን መባሉ በኢየሩሳሌም አገልግሎት ሲከናወንበት የነበረው ቦታ ዴር ሱልጣን በመሆኑና ትርጓሜውም የንጉሥ ገዳም ማለት ስለሆነ፤
2ኛ. ስደተኛው መድኃኔ ዓለም፦ ስደተኛ መባሉ ከጃንሆይ ጋር ከአገር አገር አብሮ በመሰደዱ፤
3ኛ. ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም፦ ምስካየ ኅዙናን መባሉ የኅዙናን መመኪያ በመሆኑ ነው።
​ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም የሚለውን ስያሜ ያገኘው የመድኃኔ ዓለም ታቦት በቤተ ሳይዳ ቆይቶ አሁን ያለበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በ1940 ሚያዝያ 27 በግርማዊነታቸው የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ።
​በኋላ በ1942 ሚያዝያ 27 ተጠናቆ ታቦተ ሕጉ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ወቅት ግርማዊነታቸው ምስካየ ኅዙናን የሚል ሥያሜ ሰጥተውታል።
ቅዳሴ ቤቱም ዘንድሮ ለ76ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
​ይህ የመድኃኔ ዓለም ታቦት እስከ ዛሬ ድረስ በአጠቃላይ ለ123 ዓመታት አገልግሎት ሰጥቷል በመስጠት ላይም ይገኛል።
​በአሁኑ ሰዓት ገዳሙን በበላይነት በመምራት ላይ የሚገኘው የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም አስተዳደር ቦርድ ቀደምት አባቶቻችን በገዳሙ ያስቀመጡትን ሥርዓት በማስጠበቅ በሁሉም መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ምዕመናን በባለቤትነት ይገለገሉ ዘንድ ጥብቅ ክትትል እያደረገ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የመንፈሳዊ እና የዓለማዊ ትምህርትን በሚያከናውንባቸው ተቋማት ውስጥ የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት በመንፈሳዊ እና በዓለማዊ ትምህርት ለሀገር የሚጠቅሙ ትውልድን እያፈራ ይገኛል።
​ገዳሙ በመንፈሳዊው የትምህርት ዘርፍ፦
የንባብ፣ የቅዳሴ፣ የቅኔ፣ የመጻሕፍት ሐዲሳት፣ ብሉያት ተማሪዎችን እያስተማረና ለመምህርነት እያበቃ ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ መምህራንን በማፍራት ላይ ይገኛል።
​እንዲሁም በተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጠነክሩ፣ መስማት ለተሳናቸው በራሳቸው ቋንቋ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
​በዓለማዊ ትምህርት ​የገዳሙ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በበቁ አመራሮች እና የማስተማር ብቃታቸው በተረጋገጠ መምህራን ይመራ ዘንድ የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ ግምገማ አድርጎ ተገቢውን አመራር በተገቢው ቦታ በመመደብ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ መሰናዶ ትምህርት ድረስ ትውልድን እያስተማረ ለሀገር ተተኪ ምሁራንን በማፍራት ላይ ነው።
​ከዚህ በፊት በገዳሙ ተሠርተው አገልግሎት ላይ የዋሉ የልማት ተቋማት የሆኑትን ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃ፣ መካከለኛ ክሊኒክ እና የተከራዩ ክፍሎችን በማጠናከር ለምዕመናን አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ይገኛል።
​ከዚህ በተጨማሪ የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ከተመሠረተበት ትውልድን የማፍራት ዓላማ አንጻር ያሉት የልማት ተቋማት በቂ ባለመሆናቸው ለገዳሙ እና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ርስት የሚሆን ከመሬት ሥር ባለ ሁለት ወለል፣ ከመሬት በላይ ባለ አሥራ አንድ (11) ወለል ግዙፍ ሕንፃ በማስገንባት ላይ ይገኛል።
​ይህን ግዙፍ ሕንፃ ለማስገንባት የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ከስምንት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
​በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት ምዕመናን ናቸውና ሕንፃው ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምዕመናን በማስተባበር እና የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ በማዘጋጀት በተገኘው ገንዘብ ከመሬት ሥር ያለው ሁለት ወለል አርማታ ተሞልቶ ከመሬት በላይ አራተኛ ፎቅ በመገንባት ላይ ይገኛል።
​የተወደዳችሁ ምዕመናንና ምዕመናት ይህ ታሪካዊ ገዳም እያስገነባ ያለው ግዙፍ ሕንፃ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚችለው በሁላችሁም ድጋፍ ነው። ሕንፃው እስኪጠናቀቅ ድረስ ገንዘብ ያላችሁ በገንዘብ፣ ጉልበት ያላችሁ በጉልበት፣ ሐሳብ ያላችሁ በሐሳብ ድጋፋችሁን እንድታደርጉ በመድኃኔ ዓለም ስም እንጠይቃችኋለን።
• ​ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
• ​ክቡራንና ክቡራት የመድኃኔ ዓለም ወዳጆች
​በገዳሙና የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ወደ ዛሬው ታሪካዊ በዓላችን ስንመለስ
​በመንፈስ ቅዱስ በመቃኘት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት፦
​ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር
​ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች
​ብሎ በተናገረው መሠረት ግርማዊነታቸውና ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሳይለያዩ በአንድነት የጸሎት እጆቻቸውን ወደ መድኃኔ ዓለም ዘርግተው በመጸለይ ወራሪው ፋሽስት ጣሊያንን ድል አድርገዋል።
​የጥንት አባቶቻችን ከባሕር ማዶ ተሻግሮ የመጣ የሚታይ ጠላትን በኃይለ እግዚአብሔር ድል አድርገው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበር ባሕልና ቋንቋችን እንዲሁም ሃይማኖታችን ሳይበረዝ ለእኛ እንዲደርስ አድርገዋል። በመሆኑም በበዓሉ እግዚአብሔር በረድኤቱ ቤተ ክርስቲያናችንን እና ሀገራችንን የጠበቀበትን መንገድ እያሰብን በምስጋና የምናከብረው ነው።
​ስለዚህ የተወደዳችሁ ምዕመናን አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን ባሕልና ታሪክ ጠብቀን ለሚመጣው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል።
​በዓሉን በዓለ ሰላም፣ በዓለ ፍሥሐ ያድርግልን።
​መድኃኔ ዓለም አምላካችን ሀገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን
ሕዝባችንን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ይሰውርልን
​አሜን!!!
​ሚያዝያ 27/08/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
© EOTC tv

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/0013.jpg 640 449 eotceth https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/eotceth-logo2.svg eotceth2026-05-05 09:15:012026-05-05 09:15:01ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም የ76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት እና በጀግኖች አባቶቻችን ለተገኘው 85ኛው የኢትዮጵያ የድል በዓል ያስተላለፉት መልዕክት
Search Search

Recent Posts

  • የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ትርጓሜ ምስክር ት/ቤት በባሕር ዳር ከተማ ለሚያስገነባው “የሕክምና መንደር” የመሠረት ድንጋይ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተቀመጠ።
  • የላሊበላ ቅርሶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ውይይት ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።
  • በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) እና የዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ለአስተዳደር ጉባኤው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ እየሠራ ያለውን የተለያዩ የጥናት ሰነዶች አቀረበ፡፡
  • የቤቶችና ሕንጻዎች ልማት ድርጅት ሠራተኞቹን አመሰገነ።
  • “ተመራቂዎች በየተሰማሩበት የስምሪት መስክ ሁሉ እንደ መብራት ሊያበሩ ይገባል” ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ

Archives

  • July 2026
  • June 2026
  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • January 2026
  • December 2025
  • August 2025
  • July 2025
  • June 2025
  • March 2025
  • February 2025
  • January 2025
  • December 2024
  • November 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • July 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • April 2024
  • March 2024
  • February 2024
  • January 2024
  • December 2023
  • November 2023
  • October 2023
  • September 2023
  • August 2023
  • July 2023
  • June 2023
  • May 2023
  • April 2023
  • March 2023
  • February 2023
  • January 2023
  • December 2022
  • October 2022
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: EOTC TV | የሕንጻዎችና የቤቶች አስተዳደር ድርጅት ትንሣኤ Link to: EOTC TV | የሕንጻዎችና የቤቶች አስተዳደር ድርጅት ትንሣኤ EOTC TV | የሕንጻዎችና የቤቶች አስተዳደር ድርጅት... Link to: የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም 76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በድምቀት ተከበሮ ዋለ Link to: የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም 76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በድምቀት ተከበሮ ዋለ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም 76ኛ ዓመት...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top