የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት የውል እድሳት አገልግሎትን በዘመናዊና ቀልጣፋ ሲስተም መስጠት ጀመረ።
ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም |የሕዝብ ግንኙነት መምሪያየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት፣ ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል አሠራርና የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት በመዘርጋት የ፳፻፲፱ ዓ.ም. የደንበኞች ውል እድሳትን በታላቅ እመርታ መጀመሩን ይፋ አደረገ። ድርጅቱ የሚያስተዳድራቸውን የንግድ እና የመኖሪያ ቤት ተከራይ ደንበኞቹን የውል እድሳት አገልግሎት ከሐምሌ ፩ ቀን ጀምሮ በይፋ መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ ሂደቱ እስከ ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል።
ድርጅቱ ተገልጋዮችን ማዕከል ያደረገ ሥር ነቀል የአሠራርና የቴክኖሎጂ ሽግግር (Digital Transformation) በማድረጉ ምክንያት፣ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ከፍተኛ እመርታ ተመዝግቧል። ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር በተንዛዙ ሂደቶች የተሞላ በመሆኑ፣ ደንበኞች የኪራይ ውል ለማደስ ብቻ በትንሹ ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት (ከ15 እስከ 30 ቀናት) የሚወስድባቸው ከመሆኑም በላይ ለተደጋጋሚ መጉላላትና እንግልት ይዳረጉ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ቢሮክራሲ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ዘመናዊ የዲጂታል ሲስተም በመዘርጋቱ፣ ባለጉዳዮች የሚጠበቁባቸውን መሠረታዊ ሰነዶች ብቻ አሟልተው ሲገኙ፣ ምንም ዓይነት ወረፋና መደርደር ሳይኖርባቸው ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ባለው እጅግ አጭር ጊዜ ውስጥ ውላቸው ተሻሽሎ፣ ታትሞና ተፈርሞላቸዉ በታላቅ አክብሮት እንዲሸኙ እየተደረገ ይገኛል።
ይህንን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግም፣ ተቋማዊ አሠራሩ ከባንክ የክፍያ ሥርዓት ጋር በቀጥታ እንዲተሳሰር ተደርጓል። ይህም በመሆኑ ምክንያት ደንበኞች ቀደም ሲል ይደረግ እንደነበረው ገንዘብ ለመክፈልና ደረሰኝ ለማስመታት ወደ ድርጅቱ መምጣትና በየቢሮው መንከራተት ሳይኖርባቸው፣ ባሉበት ሆነው በባንክ አማካኝነት ክፍያቸውን በቀላሉ እንዲፈጽሙ ተደርጓል። ይህ ቴክኖሎጂን ያቀናጀ አሠራር የምዕመናንንና የደንበኞችን ውድ ጊዜና ጉልበት በከፍተኛ ደረጃ ከመቆጠቡም በላይ፣ ተቋሙ ለተገልጋዮቹ የሰጠውን የላቀ የክብር ደረጃ የሚያሳይ ሕያው ማረጋገጫ ሆኗል።
ቀደም ሲል በተቋሙ ውስጥ የተደራጀ የእንግዳ መቀበያና መረጃ ሰጪ (Reception) ክፍል ባለመኖሩ ምክንያት፣ ባለጉዳዮች የሚፈልጉትን አገልግሎት በየትኛው ቢሮና በየትኛው የሥራ ክፍል እንደሚያገኙ ግልጽ መረጃ ባለማግኘት ለከፍተኛ መጉላላትና ግራ መጋባት ይዳረጉ ነበር። ይህንን ክፍተት በዘላቂነት ለመቅረፍ ተቋሙ ባደረገው አዲስ መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ የእንግዳ መቀበያ ማዕከል ያቋቋመ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ተገልጋዮች ገና ወደ ሕንፃው መግቢያ ሲደርሱ በሰለጠኑ ባለሙያዎች በታላቅ አክብሮትና ቀናነት አቀባበል ይደረግላቸዋል።
ማዕከሉ ወደ ቢሮው ለሚመጡ እንግዶች በሙሉ ወዴት መሄድ እንዳለባቸውና ምን ምን ሰነዶችን ማቅረብ እንደሚገባቸው ፈጣን ኦረንቴሽንና ግልጽ መረጃ የሚሰጥ በመሆኑ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን እጅግ ያቀላጠፈውና ተንዛዛውን አሠራር ያስቀረ ሆኗል። ይህንን ሥር ነቀል የባህልና የሥራ አካባቢ ለውጥ (Organizational Culture Shift) ተከትሎ፣ በተቋሙ ተገኝተው የተስተናገዱ ደንበኞች በሙሉ ካለፈው ዓመታት መጉላላት በመላቀቃቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታና የላቀ የዕርካታ (Customer Satisfaction) አስተያየታቸውን በከፍተኛ አድናቆት እየገለጹ ይገኛሉ።
በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የተቋሙ የመኖሪያ ቤት ተከራይ የሆኑት አቶ አውላቸው አሰፋ ሲናገሩ፦ “ከዚህ በፊት ከ6 እስከ 7 ጊዜ በላይ ውል ሞልቼ አውቃለሁ፤ በዚህ ፍጥነት ግን ተስተናግጄ አላቅም። ዛሬ በመጣሁ በ10 ደቂቃ ውስጥ ብቻ ሁሉንም ነገር ጨርሼ ወጥቻለሁ። የቢሮው ሁኔታ በጣም የሚገርም ነው፤ ከበር ጀምሮ ያለው የእንግዳ አቀባበል የተለየና ቢሮው እጅግ ዘመናዊ ሆኖ የታደሰ ነው። አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ከመጡ በኋላ በፊት በአእምሯችን ላይ የነበረውን መጥፎ አሠራር የሚያስቀር ትልቅ ለውጥ እያየን ነው” ብለዋል።
ሌላኛው የተቋሙ ደንበኛ መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ በበኩላቸው ድርጅቱ የሚገኝበት የ4 ኪሎ አካባቢ የከተማዋ እንብርት መሆኑን ጠቅሰው፦ “ቢሮዎቹ የአካባቢውን ስታንዳርድ በጠበቀ መልኩ ታድሰውና ዘመናዊ በሆነ አሠራር ደንበኛን እያስተናገዱ ይገኛሉ። እኔ ዛሬ ውል ለመውሰድ መጥቼ በ30 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የታደሰውን ውል ተቀብያለሁ። ይህ ዘመኑን የዋጀና በቤተ ክርስቲያናችን ልማት ላይ እንደ ማሳያ የሚወሰድ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት ስለሆነ እጅግ ደስ ብሎኛል፤ ለዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ስዩማን እስክንድርና ለሥራ ባልደረቦቻቸው መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በተቋሙ ቀደም ሲል ያገለግሉ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ደንበኛ የሆኑት መልአከ ሕይወት ቀለመወርቅ በበኩላቸው በተደረገው ለውጥ መደመማቸውን ገልጸው፦ “አመታዊ የኪራይ ውል አሰጣጡ በአጭር ደቂቃ ውስጥ መጠናቀቁ ደንበኞች ይማረሩበት የነበረውን ማንዛዛት አስቀርቷል። ጥያቄ ስንጠይቅ ወዲያውኑ መፍትሔ ማግኘታችን በተቋሙ ውስጥ ያለውን የተለየ ለውጥ ያሳያል። ሌላው ትልቁ ስኬት የሕንፃው እድሳት ከድርጅቱ ወጪ ሳይወጣ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር መከናወኑ ነው። ሠራተኛው በጥሩ መሪ ሥር ተናቦ እየሠራ ነው፤ ሥራ አስኪያጁን ስንጠይቅ ሥራን ለነገ አያሳድሩም፤ በዚህም ሥራ አስኪያጁንና ሠራተኞቹን በሙሉ አደንቃለሁ” ብለዋል።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት በአሁኑ ወቅት እያሳየ ያለው ሥር ነቀል የአሠራር ለውጥ፤ ተቋሙ ካለበት አሮጌና የተንዛዛ ቢሮክራሲ ወጥቶ ወደ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ዲጂታላይዝድ ወደሆነ አሠራር መሸጋገሩን በተግባር ያሳየበት ሆኗል። ከአራት ሳምንታት እንግልት ወደ 20 ደቂቃዎች መስተንግዶ የተደረገው የጊዜ ቅነሳ፣ ደረጃውን የጠበቀ የእንግዳ መቀበያ (Reception) ማቋቋም መቻሉ እና ከባንክ የክፍያ ሥርዓት ጋር የተገነባው ትስስር ተቋሙ ለደንበኞቹ የሰጠውን የላቀ የክብር ደረጃ የሚያረጋግጡ አበይት ማሳያዎች ናቸው።
ይህ በድርጅቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው ደንበኛ ተኮር አገልግሎትና የቢሮዎች መታደስ፤ በአዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ መሪነትና በሥራ ባልደረቦቻቸው ቁርጠኝነት የመጣ መሆኑን ተገልጋዮች በታላቅ ዕርካታ መስክረዋል። ለውጡ ከድርጅቱ ካፒታል ላይ ምንም ዓይነት ወጪ ሳይደረግ፣ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር የተከናወነ መሆኑ ደግሞ የአመራሩን ስልታዊና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሥራ መሪነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል።
የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት ይህንን የተጀመረውን የልማት፣ የማዘመንና የቀናነት ጉዞ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ያረጋገጠ ሲሆን፤ ይህ ስኬታማ ተሞክሮ በሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ ተቋማትና መዋቅሮች ዘንድ እንደ መልካም ተሞክሮ (Best Practice) የሚወሰድና የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት ይበልጥ የሚያፋጥን መሆኑ ታምኖበታል።