የሀገር አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ሥልጠና በወንጪ ሐይቅ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ታሪካዊ ጉብኝት በማድረግ ተጠናቀቀ።
ሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
“የሕዝብ ግንኙነት ስኬት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል ለሀገር አቀፍ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በከፍተኛ ዝግጅት ሲሰጥ የሰነበተው ፫ኛው ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለት በወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ጉብኝት ተጠናቋል።
የዚሁ ታሪካዊ ሥልጠና ማጠቃለያ ይሆን ዘንድ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በወንጪ ወረዳ በሚገኘው ታዋቂው የወንጪ ሐይቅ ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም ልዩ የጉብኝት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
ይህ ታላቅ የጉብኝት እና የመስክ ውይይት መርሐ ግብር በወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሊከናወን የቻለበት ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሀገረ ስብከት በመሆኑና መርሐ ግብሩን በዚህ ታሪካዊ ሥፍራ ቢከናወን የሥልጠናውን ማጠቃለያ ይበልጥ ልዩና ታሪካዊ መርሐ ግብር ስለሚደርገው በልዩ ሁኔታ መመረጡ ተገልጧል።
ሠልጣኞቹ በጉብኝቱ ወቅት የወንጪ ሐይቅ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሠረተና የታላቅ መንፈሳዊ ታሪክ ባለቤት መሆኑን የተረዱ ሲሆን አካባቢው በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር የቱሪስት መስህብ ሆኖ መሠራቱን ተከትሎ ወደ ሥፍራው ለጉብኝት የሚጓዙ ጎብኚዎች ጥንታዊውን የቅዱስ ቂርቆስ ገዳምን እንዲጎበኙ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ጥንታዊ መሠረቱን ሳይለቅ በአዲስ መልክ እንዲሠራ ክቡር የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚሠራ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።
በገዳሙ የሚከናወኑትን የልማት ሥራዎች በርካታ ብፁዓን አባቶች የጎበኙትና ለግንባታ ሥራው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን በገዳሙ ውስጥ በርካታ አህጉራዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ታላላቅ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎቹ ተመልክተዋል።
ሠልጣኞቹ በገዳሙ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ፣ የሙዚየም ግንባታ፣ የቤተ መቅደስ ግንባታ፣ የቤተልሔም ሕንጻ እንዲሁም አጠቃላይ የቅጥርና የመሠረተ ልማት ግንባታ ሂደቶች በፍጥነት በመገንባት ላይ መሆናቸውን ተመልክተዋል። በጉብኝቱ ወቅት ስለ ገዳሙ ጥንታዊ አመሠራረት፣ ስለ ነበረው ታሪክና አሁን ስላለው ሁለንተናዊ የዕድሳት ሂደት ሰፊና ጥልቅ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ ሠልጣኞቹም ካዩት ታላቅ መንፈሳዊ ቅርስና የልማት እንቅሰቃሴ በመነሳት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታና አበረታች አስተያየት በስፋት ገልጸዋል።
ከዚሁ መንፈሳዊ የጉብኝት መርሐ ግብር ማጠቃለያ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ በሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ አማካኝነት ለሠልጣኞቹ የተሳትፎ የምስክር ወረቀት በታላቅ ሥነ ሥርዓት ተበርክቶላቸዋል።
የመምሪያው ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ለሠልጣኞቹ ባስተላለፉት ጥብቅ መመሪያ፤ ኃላፊዎቹ በሥልጠናው ወቅት ያገኙትን ከፍተኛ ዕውቀትና ክህሎት ወደየአህጉረ ስብከታቸው በሚመለሱበት ወቅት ያለምንም መዘግየት ወደ ተግባር እንዲቀይሩት አሳስበዋል። አያይዘውም ተሳታፊዎቹ የእውነት ጠበቃ በመሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ድምፅ እንዲሆኑ፣ በተመደቡበት የኃላፊነት ቦታና አገልግሎት ሁሉ ሳይታክቱና ሳይሰለቹ በርትተው እንዲሠሩ፣ እንዲሁም ለሃይማኖታቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው በጽናት እንዲቆሙ በብርቱ ቃል አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የመምሪያው ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ይህ አገር አቀፍ የሥልጠናና የጉብኝት መርሐ ግብር እጅግ የተሳካ፣ ፍሬያማና ውጤታማ ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ ሙሉ የገንዘብ ወጪውን በመሸፈን የላቀ ክርስቲያናዊ አጋርነቱንና ታሪካዊ ድጋፉን ላሳየው ለአሐዱ ባንክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ከፍተኛ ምስጋናቸውንና አድናቆታቸውን አቅርበው መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል።
ፎቶ Eotc tv