የጋርመንት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አዲስ የሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፤ ከ5.7 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የልማት ሥራዎች ተመረቁ።
ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም.የጋርመንት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአዲስ ለሚገነባው የሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተገኝተው የመሠረት ድንጋዩን የባረኩ ሲሆን፣ የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችንም መርቀዋል።
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ባቀረበው ልማታዊ ሪፖርት መሠረት፣ ቤተ ክርስቲያኑ በ1997 ዓ.ም. በአነስተኛ መቃኞ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው እያደገ የመጣ ሲሆን፣ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 1.34 ሚሊዮን ብር ክፍያ በመፈጸም 1,350 ካሬ ሜትር ተጨማሪ ቦታ ወደ ደብሩ ይዞታ እንዲካተት አድርጓል።
በዕለቱ በብፁዕነታቸው የተመረቀውና ቀደም ሲል በአፈርና በገረጋንቲ ተራራ ተሸፍኖ ለጎርፍ አደጋ ተጋልጦ የነበረው የቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት፣ በባለሙያ በተጠናው መሠረት ምዕራባዊ አቅጣጫውን የጠበቀና ደረጃውን የጠበቀ የመጠለያ፣ የቴራዞ፣ የኮብልስቶን ንጣፍና የውኃ ፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎች ተከናውነውለታል። ለነዚህ የዐውደ ምሕረት ማሻሻያና መጠለያ ሥራዎች በሰበካ ጉባኤውና አዲስ በተዋቀረው የልማት ኮሚቴ አማካኝነት፣ ከምዕመናን በዓይነት ከተገኘው ድጋፍ ጋር ተደምሮ በአጠቃላይ 5,788,538.92 (አምስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰማንያ ስምንት ሺሕ አምስት መቶ ሠላሳ ስምንት ብር ከዘጠና ሁለት ሳንቲም) ወጪ መደረጉ ታውቋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፤ የመጀመሪያውና ዋናው ልማት ወንጌል እንደሆነ ዐፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። አክለውም “ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቁጥር መጨመር ምላሽ የሚሰጥና ለትውልድ የሚተላለፍ አዲስ ሕንጻ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ባርከን አስቀምጠናል፤ ነገር ግን አዲስ ሕንጻ ሲታነጽ በዲዛይንና በጥራት ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል። ብዙ ገንዘብ ወጥቶበት ከተሠራ በኋላ የዲዛይን ችግርና የቦታ መጥበብ እንዳያጋጥም ሥራውን በቶሎ በመጀመር በጥራት እንዲያጠናቅቁ መመሪያ የሰጡት ብፁዕነታቸው፣ ቤተ መቅደስ ማነጽ የሚቻለው እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው ብቻ በመሆኑ ምዕመናኑ የተሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው ጊዜ ሳያባክኑ እንዲረባረቡ አሳስበዋል።
የዕለቱን ትምህርተ ወንጌል የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “እግዚአብሔር በእውነት በዚህ ስፍራ አለ” (ዘፍ 28፥16) የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ዓለማየሁ ተፈራ በበኩላቸው፤ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጧቸውን በርካታ አብያተ ክርስቲያናት መመሪያ በመስጠት ብቻ ሳይሆን በቅርበት ክትትል ስለሚያደርጉ፣ በጥራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት እንዲበቁ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ግንባታቸው ዘግይቶ የነበሩ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተጠናቀው መመረቃቸውን አስታውሰዋል።
በዕለቱ በደብሩ ለተሠሩ የልማት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምዕመናን የሽልማትና የምስጋና ሰርተፍኬት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩማን ተስፋዬ ለሜቻ፣ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ መጋቤ ወንጌል ሄኖክ ታዬ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ጳውሎስ ከበደ፣ የደብሩ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩም አክሊሉ፣ የደብሩ የሥራ ኃላፊዎች፣ ማኅበረ ካህናትና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቅቋል።
Miidiyaa Biyya Lallabaa Shaggar/የሸገር ሀገረ ስብከት ሚዲያ/