አሐዱ ባንክ ላደረገው ሁለተናዊ እገዛ በቋሚ ሲኖዶስ የእውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበረከተለት።
ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ምአዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ መመሪያ ሰጪነት በሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አዘጋጅነት ሐምሌ 9 እና 10 ቀናት 2018ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኀላፊዎች የምክክርና የውይይት መርሐግብር ዘርፈ ብዙ ግንዛቤዎችን በማስጨበጥ የተጠናቀቀ ሲሆን ይህንን የሥልጠና መርሐ ግብር ሙሉ ወጪ በመሸፈን አስተዋጽኦ ላደረገው ለአሃዱ ባንክ አክሲዮን ማኅበር እና መምሪያውን በዘመናዊ መልኩ በማደራጀት ትብብር ላደረጉ አካላት እንዲሁም ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የሥልጠና መርሐ ግብሮች ላይ ለተሳተፉ ምሁራን የቤተክርስቲያን ልጆች በዛሬው እለት የምስጋና ምስክር ወረቀት ስጦታ ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ተበርክቶላቸዋል።
በመርሐ_ግብሩ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የመምሪያው ዋና ኀላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ ቤተክርስቲያን
ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ሀቀኝነትን መሰረት ያደረገ፣ተቋም ተኮር የሆነ የሕዝብ ግንኙነት ሥራን ለመሥራት የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጥን ዓላማው ያደረገው ሥልጠና በቅርቡ መሰጠቱን አስታውሰዎ የሥልጠናውን ወጪ እንዲሸፍን ለአሐዱ ባንክ የቀረበው ጥሪ ባንኩ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሥልጠናውን በስኬት እንድናከናውን ስላደረገን በቅዱስነትዎና በቋሚ ሲኖዶስ ፊት ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
በመቀጠልም ሕዝብ ግንኙነት ለአራት ተከታታይ ዓመታት በሚያደርጋቸው ስልጠናዎች እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ የመምሪያው አጋር በመሆኑ ያገዙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በዚሁ እለት እውቅና የምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው የተደረገው ቀጣዩን ሥራችንን ስኬታማ ለማድረግ ስለሆነ ላበረከታችሁልን አስተዋጽኦ ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ ብለዋል።
በዚሁ ጊዜ ብፀዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት የሰማነው ሁሉ ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ ነው። ቤተክርስቲያን የሁላችንም ስለሆነች ቤተክርስቲያንን መርዳት የሁላችንም ግዴታ ነው ። በቤተክርስቲያን ላይ የሚነሱ አጸያፊ ስም ማጥፋቶችን ለመከላከልም ይሁን የቤተክርስቲያን ትክክለኛ አንደበት ለመሆን የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ እጅግ ደስ የሚል ነውና ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ስለሆነ ለሥልጠናው ስኬት ድጋፍ ላደረጋችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ይስጥልን ብለዋል።
ከቅዱስነታቸው መልዕክት ቀደም ብሎ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የመምሪያውን ዋና ኀላፊ በማመስገን ጀምረው በውይይቱ መርሐግብሩ ቤተክርስቲያን ሊያስከብር የሚችል ምክክር እንደተደረገ ምስክርነታቸውን ሰጥተው በቀጣይም በቤቶችና ሕንጻዎችም ይሁን በሕዝብ ግንኙነት መምሪያ የሚታየው ለውጥ እንዲቀጥል አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የአሐዱ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ “ከብዙኃን ለብዙኃን” በሚለው ሥራችን መሠረት ቤተክርስቲያን ለምታደርገው ማንኛውም ልማት እገዛ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራችን ነው ብለዋል።(ፎቶ Eotc tv)