የቄለም ወለጋ ሃገረ ስብከት ማህበረ ምዕመናን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ለብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ምስጋና አቀረቡ።
መስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ —ኢትዮጵያ
የቄለም ወለጋ ሃገረ ስብከት ማህበረ ምዕመናን በሀገረ ስብከቱ ተፈጥረው ለነበሩ አስተዳደራዊ ችግሮች ቅዱስ ሲኖዶስ ፈጣን ምላሽ በመሰጠቱ ልባዊ ምስጋናቸውን አቀረቡ።
በሀገረ ስብከቱ በተለያዩ ጊዜያት አጋጥመው በነበሩ አስተዳደራዊ በደሎች የተነሳ ማህበረ ምዕመኑ ጥያቄዎቹን ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክርስቲያን በማቅረብ ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል። ጉዳዩን በንቃት የተከታተሉት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ አጣሪ ልዑክ በመላክ ሁኔታውን በማጣራት ለሕዝበ ክርስቲያኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምዕላተ ጉባኤ
እንዲቀርብ አድርገው ባለፈው የግንቦት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ ሁኗል።
በዚህም መሰረት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የቡኖ በደሌ ሃገረ ስብከትን በበላይነት እንደያዙ የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን እንዲመሩ ተወስኖ ብፁዕነታቸው አዲሱ ሀገረ ስብከታቸው ከገቡ ጀምሮ፦የተራራቁ አካላትን በማቀራረብ፣
የተጣሉትን በማስታረቅ እና ያኮረፉትን በመመለስ፣
የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት እና ሀገረ ስብከቱን ወደ ቀደመው ሰላምና ልዕልና በመመለስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በዚህም የተነሳ ምዕመኑ ሰላሙ አጠናክሮ ወደ መንፈሳዊ ሕይወቱ በመመለስ ቤተ ክርስቲያኑን በንቃት በመጠበቅና በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።
ስለሆነም የቅዱስ ሲኖዶስከ ምልአተ ጉባኤ የቄለም ወለጋ ማህበረ ምዕመናን ድምፅ በመስማት ለቤተክርስቲያንና ለምዕመናን የሚበጅ ውሳኔ በማስተላለፉ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ — ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ — የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ፤ ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ — የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
እንዲሁም ለመላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ምስጋና የሚያቀርቡ በብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሚመሩ ልዩ የልዑካን ቡድን በመሰየም በዛሬው ዕለት (መስከረም 13 ቀን)ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቤተክህነት የላኩ ሲሆን ልዑካኑ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሲደርሱ ብፁዕ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቀባበል አድርገውላቸው ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩክ ጋር ተገናኝተው የልጅነት ሥጦታቸውን አበርክተው ቡራኬ ተቀብሏል።
ቅዱስነታቸው የቄለም ወለጋ ሕዝበ ክርስቲያንን ወክለው የተገኙትን ልዑካን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፤ «የቄለም ወለጋ ሕዝበ ክርስቲያን ጠንካራና ለእምነቱ ሟች የሆነ ሕዝበክርስቲያን ነው፤ ስለ መጣቹም ከልብ አመሰግናለው አሁንም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በእምነቱ ጸንቶ መቀጠል አለበት» በማለት አባታዊ መልእክትና ቡራኬ ሰጥተው ፤ መርሐ ግብሩም በሰላም ተጠናቋል።