ርቀት ያልገደበው የሁለቱ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት ግንኙነት ።
በመምህር አቤል አሰፋ
የምሥራቅ ካቶሊኮስ እና የማላንካራ ሜትሮፖሊታን የሆኑት የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ በሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ከመስከረም 14–18 ቀን 2019 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግብዣ መሠረት ቅዱስነታቸው በታላቁ የቤተክርስቲያንናችን የመስቀል ደመራ በዓል በመገኘት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጋር በመሆን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ያስተላልፋሉ ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት በዚህ ጉብኝት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አቀባበል ተደተደርጎላቸዋል። በዚሁ ካቴድራል ሥርዓተ ጸሎት አድርሰዋል ። ቅዱስነታቸው በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት በሕንድ እና በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን መንፈሳዊ አንድነት በጎላ ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ሁለቱም የእህትማች አብያተ ክርስቲያናት የኦሬንታል ኦርቶዶክስ ቤተሰብ አባላት እንደመሆናቸው መጠን፣ በተመሳሳይ ዶግማ እና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሆነው በባህላቸው እና ቋንቋቸው የተለያዩ ናቸው።
የሁለቱ አብያተክርስቲያናት ግንኙነት ታሪካዊ መሠረት አለው። ከዚህ ታሪካዊ ግንኙነት በይፋዊቱ የሚጠቀሰው በ1965 (እ.ኤ.አ) ካቶሊኮስ ባስሊዮስ ኦገን ፩ኛ በአዲስ አበባ በተካሄደው ታሪካዊ የኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳታፊ ነበሩ። በ2013 (እ.ኤ.አ) ካቶሊኮስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ፪ኛ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፩ኛ የፓትርያርክነት በዓለ ሢመት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር። በ2016 (እ.ኤ.አ) ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ወደ ሕንደኬ ኬርላ ተጉዘው ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል።
የብፁዕ ወቅዱስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ ጉብኝት ይህንን ርቀት ያልገደበው የወንድማማችነት እና የእህትማችነት ግንኙነት ያስቀጥላል።
የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቋንቋ ባህል እና ትውፊት ቢለያዩም በዶግማ ባላቸው አንድነት በአንድ መንበር ቀድሰው ምስጢረ ቁርባንን የሚካፈሉ እምነት አንድ ያደረጋቸው አብያተክርስቲያናት ናቸው።
የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ
ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎት ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከዚህ ዓለም ድካም ባረፉት በቀድሞው የቤተክርስቲያናችን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት ተገኝተው ጸሎተ ፍትሐት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ ” በዓለም ዙሪያ ባደረግኳቸው ሐዋርያዊ ጉዞዎች ሁሉ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሞቅ ያለና ልብን የሚነካ አቀባበል ያደረገልኝ የለም። ዛሬም በካቴድራሉ የተደረገልኝ አቀባበል፣ የቀረበው ዝማሬና ክብር ልባችንን በጥልቅ ነክቶታል” ሲሉ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተደረገላቸው አቀባበል ላይ ተናግረዋል ።
በየራሳቸው ትውፊት እና ሥርዓተ ቅዳሴ ያላቸው የሕንድ እና የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳን አባቶች በቦሌ ደብረ ሣሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል በአንድ መንበር፣ በአንድ የኦርቶዶክስ እምነት፣ በአንድ ሥርዓተ ቁርባን በሁለት ቋንቋዎች ቀድሰው ከቅዱሱ መለኮታዊ ምስጢር በአንድነት ይካፈላሉ። ይህም ግንኙነቱ ከተቋማዊነት አልፎ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ፍፁም መንፈሳዊ አንድነታቸውን ያሳያል።
ይህ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት በሁለቱ እህትማማች አብያተ ክርስቲያኖቻችን መካከል ያለውን ጥብቅ ግንኙነት ያሳድጋል ።
የኢትዮጵያ የሥነ መለኮት ተማሪዎች በሕንድ ሴሚናሪየሞች ከፍተኛ ትምሕርታቸውን እንዲከታተሉ ዕድል የሰጠው የኢትዮጵያ እና የሕንድ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት ግንኙነት ፤ በኢትዮጵያ መንፈሳዊ ኮሌጆችና በዩኒቨርስቲዎች የሕንድ የሥነ መለኮት ሊቃውንት በመምህርነት እንዲያገለግሉ ዕድል ይሰጣል። ይህም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ ለመጡት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሴሚናሪ እና ኮሌጆች መልካም ዜና ከመሆኑም በላይ የጠቅላላውን የኦሬንታል ኦርቶዶክስ ቤተሰብ አንድነት እና የጋራ ግንኙነት ያጠናክራል ።
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ግብዣ ወደ ሀገራችን የመጡት የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ የተመራው ልዑክ በርዕሰ አድባራት በእንጦጦ ማርያም፣ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም እና በሰበታ ቤተ ደናግል ጠባባት ገዳም ሐዋርያዊ ጉብኝት ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል። ልዑኩ ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አቻው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደርጋል ።
የቅዱሳን ፓትርያርኮቻችን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ ቡራኬ አይለየን።©Eotc tv