ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጆርዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የኦርቶዶክስ ልኡካን ቡድንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
መስከረም 19/2019 ዓ.ም. አዲስ አበባ-ኢትዮጵያብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ፤ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የጆርዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የጆርዳን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልኡካን ቡድንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ልኡካኑ ቅዱስነታቸውን በአካል በማግኘታቸው እና ቡራኬ በመቀበላቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸው ጆርዳን የክርስትና እምነት የተስፋፋባት፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመጠምቀያ ቦታ የሆነው የዮርዳኖስ ወንዝ የሚገኝባት እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ታሪካዊ ቦታዎች መገኛ መሆኗን አንስተዋል።
አያይዘውም ሀገሪቱ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ያለምንም የሃይማኖት ግጭት በፍቅር የሚኖሩባት፣ በሠርግ፣ በሐዘን እና በበዓላት ወቅትም አብሮ በመብላትና በመጠጣት የሚታወቅ ውብና የሰላም አብሮነት ያላት ምድር መሆኗን ገልጸዋል።
ጆርዳን በዓለም ላይ ካሉ ሃይማኖቶች መገኛ እና መተላለፊያ ማዕከላት አንዷ እንደ መሆኗን የጠቀሱት ልዑካኑ አሁን ያሉት የሀገሪቱ ንጉስ ሁለተኛ አብዱላህ (King Abdullah II) ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአምልኮ ቦታ መፍቀዳቸውን ጠቅሰው ይህ ታሪካዊ ቦታ በቅዱስነታቸው ዘመን ተባርኮ ቤተክርስቲያን እንዲገነባበት እና የሁለቱ አገራት ማለትም የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ትውፊትና አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብና ከቅዱስነትዎ ቡራኬ ለመቀበል መጥተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት ቤተ ክርስቲያናችንንና አገራችንን ለመጎብኘት በመምጣታችሁ እጅግ ተደስተናል፤ እኔ ኢየሩሳሌም በነበርኩበት ወቅት ጆርዳንን በቅርበት ስለማውቃት የገለጻችሁት ሁሉ እውነት ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያንም በዚያ ይኖራሉ፤ ኢትዮጵያንና ጆርዳንን የሚያስተሳስሯቸው ታሪካዊ እውነታዎች እንዳሉም አውቃለሁ» ብለዋል። አያይዘውም ከአካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በመመካከር ይህ የተቀደሰ ሐሳብ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደ ሚለወጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸውላቸዋል።
በሌላ በኩል፣ የልኡካን ቡድኑ በጠቅላይ ቤተክህነት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራአስኪያጅ እየተከናወኑ ያሉትን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የሚደነቁና የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።