የምስጋና መልዕክት
የ፳፻ ፲ወ፱ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓትና ድምቀት ተከብሮ በመዋሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች።
የ2019 ዓ/ም የመስቀል ደመራ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቲዮስ 3ኛ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርያርክ፣
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ፣ክብርት ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣አምባሳደሮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በታላቅና ደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት ተከብሮ ውሏል።
በዓሉ በተዋበና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ዝናብና ቁር ሳይበግረው በጽናትና ፍጹም በሆነ መንፈሳዊነት በዓሉን ማክበሩ እጆግ የሚያስደንቅ ሲሆን መርሐ ግብሩ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዲችል ተረኛው ደብር፣ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ልጆቻችንና በበዓሉ ላይ ልዩልዩ መንፈሳዊ ትርኢት ስታቀርቡ የነበራችሁ በሙሉ ላሳያችሁት ጨዋነት የተሞላው መታዘዝ ቅድስት ቤተኮርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።
ሕዝበ ክርስቲያንኑ በዓሉ ወደ ሚከበርበት መስቀል አደባባይ በሚጓዝበት ወቅት ፍጹም ጨዋነትና መንፈሳዊነትን በተላበሰ መልኩ ለመንግስት የጸጥታ አካላት ትብብር በማድረግ፣ራሱም ጸጥታ አስከባሪና ተባባሪ በመሆን ያሳየው ድንቅ ትብብርም የሚደነቅ ሲሆን በዓሉን ከሚያውኩ ተግባራት በማራቅም ቤተክርስቲያን ከበዓሉ አስቀድማ ያስተላለፈቻቸውን የጥንቃቄ መልዕክታት በሚገባ በመፈጸም ታዛዥነቱን በማስመስከሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች።
በሌላ በኩል በዓላችን ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ የፌዴራልና የክልል የደህንነትና የጸጥታ አካላት፣የአዲስ አበባ ሰላም ጸጥታ ቢሮና የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች የጸጥታ አካላት ሙያዊ ግዴታችሁን በሚገባ በመወጣት ያደረጋችሁት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነውና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ስታቀርብላችሁ በከፍተኛ ደስታ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በዓሉ እጅግ ደማቅ በሆነ መልኩ እንዲከበር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማለትም የስቴጅ፣የክብር እንግዶች ወንበር፣አካባቢውን የማስዋብ ሥራና የድምጽ ማጉያዎችን ወጪ በመሸፈን እንዲሁም ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ሁሉ በፍጥነትና በቅንነት ምላሽ በመስጠት ላደረገልን ትብብር እያመሰገነች በተለይም ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀልጣፋ አመራር በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች ።ይህ አይነቱ መተጋገዝና የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የመስራት ልምዳችንም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ትወዳለች።
በሌላ በኩል በዓሉ ባማረና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ በጠቅላይ ቤተክህነትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የተደራጁት ዐበይትና ንዑሳን ኮሚቴዎችም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ ተቋማት ጋር በጥምረት የሰራችሁት ስራዎች እጅግ ውጤታማና ስኬታማ በመሆናቸው እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ትወዳለች።
በአጠቃላይ የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓላችን በተዋበ፣በተሳካና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ላደረጋችሁልን ተቋማት በሙሉ በተለይም በዓላችን ፍጹም መንፈሳዊ በዓል መሆኑን በዓለም መድረክ በማሳየት ደረጃ ዝናብና ቁር ሳይበግራችሁ በጽናት በመቆም በዓላችሁን በሚገባ ላከበራችሁ ኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን አደረሳች፤ በዓለ መስቀሉ የሰላም፣የደስታና የፍቅር በዓል ይሁንላችሁ በማለት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መልካም ምኞቷን ትገልጻለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፱ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ